በኦሮሚያ ክልል 3 ሺህ 732 የጎዳና ተዳዳሪ ህፃናት ከቤተሰቦቻቸው ጋር እንዲቀላቀሉ ተደረገ

72

አዳማ ታህሳስ 27/2011በኦሮሚያ ክልል 3 ሺህ 732 የጎዳና ተዳዳሪ ህፃናት ከቤተሰቦቻቸው ጋር እንዲቀላቀሉ መደረጉን የክልሉ ሴቶች ህፃናትና ወጣቶች ጉዳይ ቢሮ አስታወቀ፡፡

በክልሉ ከአንድ ሚሊዮን በላይ ህፃናት በአስቸጋሪ ሁኔታ ላይ እንደሚገኙ ተገልጿል፡፡

በኦሮሚያ ክልል ሴቶች ህፃናትና ወጣቶች ጉዳይ ቢሮ የህፃናት ቤተሰብ ማፈላለግና ማቀላቀል ከፍተኛ ባለሙያ አቶ እውነቱ ቡሼ ለኢዜአ እንደገለጹት ህፃናቱን ከጎዳና በማንሳት ለቤተሰቦቻቸው እንዲሰጡ የተደረገው ባለፉት ስድስት ወራት ውስጥ ነው።

በኤች አይ ቪ ኤድስና ተዛማጅ በሽታዎች ወላጆቻቸውን በሞት ማጣት፣ የትዳር መፍረስና ድህነት ለህፃናቱ  ወደ ጎዳና መውጣት ምክንያች መሆናቸውን ገልፀዋል፡፡ 

በኦሮሚያ ክልል በሚገኙ 335 ወረዳዎች በተደረገው የዳሰሳ ጥናት ከአንድ ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ ህፃናት በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ እንደሚገኙ ያስታወቁት ባለሙያው ወደ ጎዳና የወጡ ሌሎች ህጻናትን ወደ ቤተሰቦቻቸው ለመመለስ እየተሰራ መሆኑን አስረድተዋል።

በተጨማሪም ከተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች ወደ ኦሮሚያ ክልል በመምጣት ለጎዳና ኑሮ ተዳርገው የነበሩ 116 ህፃናትም ወደ ደቡብ ፣ አፋር፣ አማራና ሌሎች ክልሎች ተመልሰው ከቤተሰቦቻቸው ጋር እንዲገናኙ መደረጉንም አቶ እውነቱ አመልክተዋል፡፡

ከጎዳና እንዲነሱ የተደረጉ ህጻናት ወደ ቤተሰቦቻቸው ከመቀላቀላቸው በፊት የስነልቦናና የምክር አገልግሎትን ጨምሮ የስነ ምግባር ስልጠና እንዲያገኙ ተደርጓል ።

መማር ለሚፈልጉ ህፃናት ቤተሰቦቻቸው ባሉበት አካባቢ የትምህርት እድል እንዲያገኙ በመንግስት በኩል ሁኔታዎችን የማመቻቸት ሥራ እየተከናወነ መሆኑን ባለሙያው አስረድተዋል፡፡

በተያዘው በጀት ዓመት ወደ ጎዳና የወጡትን ህፃናት ከጎዳና የማንሳትና ወደ ቤተሰቦቻቸው የማቀላቀል ሥራ ቅድሚያ ተሰጥቶት እየተከናወነ መሆኑን  በሴቶች ህፃናትና ወጣቶች ጉዳይ ሚኒስቴር የህፃናት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ አለሚቱ  ዑቦንግ አስረድተዋል፡፡

በአገር አቀፍ ደረጃ ከ11 ሺህ በላይ የሚሆኑትን ህፃናት ከጎዳና ማንሳት መቻሉን የገለጹት ወይዘሮ አለሚቱ ለህጻናቱ የስነልባናና የሞራል ስልጠና መሰጠቱን ተናግረዋል፡፡

ህጻናቱ ባሉበት አካባቢ የትምህርት እድል እንዲያገኙ የማድረግ ስራ  በክልሎችና በከተማ መስተዳድሮች በኩል ትኩረት ተሰጥቶት እየተሰራ መሆኑን አመልክተዋል፡፡

መንግስት የሀገር ውስጥ ጉዲፋቻን ከማበረታታት ጀምሮ የህፃናት ማቆያ ማዕከላትን በቁሳቁስና በፋይናስ የማጠናከር የተለያዩ ፕሮጀክቶችን በመቅረፅ ዘላቂ ድጋፍ፣ ክትትልና እገዛ እየተደረገ መሆኑን ጠቅሰዋል።

ልጆች ወደ ጎዳና እንዳይወጡ  በቅንጅት መስራት የሁሉንም  ግዴታ መሆን እንዳለበት ሚኒስትር ዴኤታዋ አሳስበዋል።

በሀገር አቀፍ ደረጃ ከ3 ሚሊዮን በላይ ህፃናት ልዩ ድጋፍና እንክብካቤ እንደሚሹ  ከሴቶች ህፃናትና ወጣቶች ጉዳይ ሚኒስቴር የተገኘ መረጃ ያመለክታል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም