አለመግባባትን በማስታረቅ በአሉን በፍቅር ለማሳለፍ መዘጋጀታቸውን የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ተናገሩ

53

ታህሳስ 27/2011 በሰዎች መካከል የሚፈጠር አለመግባባትን በማስታረቅ በአሉን በፍቅር ለማሳለፍ ዝግጁ መሆናቸውን አንዳንድ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ተናገሩ።

አቶ ኤሊያስ ማሞ በልብስ ስፌት ሥራ ነው የሚተዳደሩት። “ኢትዮያውያን ጎልተን የሚንታወቅበትን  አብሮ የመኖርና የመተባበር ባህልን በተለይ በበዓላት ወቅት ወዳጅ ዘመድን የምንጠያየቅበት ነው” ይላሉ።  

አቶ ኤሊያስ ቀደም ብለው በመቆጠባቸው ሳይጨናነቁና ቤታቸው ሳይጎዳ ለበአሉ  የሚያስፈልጋቸውን ማዘጋጀታቸውን ይጠቅሳሉ።

የበአሉን መንፈሳዊና ባህላዊ እሴቶች “ስጥ ይሰጥሀል የሚለውን የመጽኃፍ ቃል ተግባራዊ በማድረግ፤  የተቸገሩ ወገኖችን በመርዳት በደስታ ለማሳለፍ አቅጃለሁ”  ነው ያሉት።  

“በአል ማለት እኛ ብቻ መብላትና  መጠጣት  ሳይሆን ከጎናችን የተራቡና የተጎዱትን ተረዳድተን መኖር ነው፤ ያንግዜ ነው የሚደምቀው” በማለትም ነው የመረዳዳት ባህሉ እንዲጠናከር የሚመክሩት።  

በአልን ስያከብሩ የሚከሰት መቀያየምና አለመግባባትን በይቅርባይነት በመፍታት  ለሰላም የድርሻቸውን ለመወጣት ዝግጁ እንደሆኑም ተናግረዋል።

አቶ ሳለአምላክ ተገኘ በከሰል ንግድ ነው ሩኖአቸውን እየመሩ ያሉት። አቅማቸው በፈቀደ መጠን ዶሮ ና ሌሎች ለበአል የሚያስፈልጉ ነገሮችን  ማዘጋጀታቸውን ነው የነገሩን።

በሚኖሩበት በአካባቢው ጉርብትና የተለመደ በመሆኑ ሁሉም እንደየአቅሙ ተከባብሮ ና ተጋግዞ  በጋራ በአልን በደስታ እንደሚያሳልፍም  ጠቅሰዋል።

በአል ሲመጣ በአከባቢያቸው  አቅማቸው በፈቀደ መጠን ያላቸውን  በማሰባሰብ   ለተቸገሩ ሰዎች እንሰሚያካፍሉም ተናግረዋል።

በተለይ በአሁኑ ሰአት “በተለያየ መንገድ ከአካባቢያቸው የተለዩ ወገኖችን እንደ ኢትዮጵያዊነታችን አቅም የፈቀደውን በማድረግ፤ በተቻለን አቅም ተጋግዘንና ተፋቅረን እንኑር” በማለት  መልእክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

በአልን በስራ እንደምታሳልፍ የገለጸችው በከተማ ጽዳት የተሰማራችው  ወይዘሪት ብርሀኔ ጌቱ፤ ለበአሉ  ቤት ያፈራውን በማዘጋጀት ከጋደኞቿ ጋር እንደሚታሳልፍ ገልጻለች።

ሌላው በከተማ ጽዳት የተሰሩት  አቶ ሸምሰዲን አማን በበኩሉ የእስልምና እምነት ተከታይ  ቢሆኑም ሰዎች በአልን ሲያሳልፉ ለበአል ያዘጋጁት የእርድና ሌሎች ተረፈ ምርቶች በልጆችና አረጋውያን ላይ ጉዳት  እንዳያደርሱ ቶሎ ከማንሳት ባለፈ ከክርስትና እምነት ተከታይ ጓደኞቻቸው ጋር  በፍቅር እንደሚያሳልፉተናግረዋል፡፡

በጡረታና ከልጆቻቸው በሚያገኙት ድጎማ የታመመን በመጠየቅና የተቸገረን በመርዳት በአልን ከወዳጅ ከዘመድ ጋር በደስታ  እንደሚያሳልፉ የተናገሩት ደግሞ  ወይዘሮ አጸደ ኃይለ ግዮርጊስ ናቸው ፡፡

“ደጅ ለሚያድሩት ወንድሞቼና እህቶቼ ያለችኝን አካፍላለሁ” ያሉት ወይዘሮ አጸደ ልጆቻቸውም ከሌሎች ሰዎች ጋር በመተባበርና በፍቅር እንዲኖሩ እንደሚመክሯቸው ነው የተናገሩት።  

ለበአል ገበያ ቅመማቅመም ሲሸጡ ያገኘናቸው ወይዘሮ ወሰኔ ማርያሜ በበኩላቸው “የበአል ግብይት  ጥሩ ነው፤ የእኔም  ልጆች ጎረቤት ያዩትን ጭምር ቢጠይቁም አቅሜን በማስረዳት በአልን በደስታ  ለማሳለፍ  ተዘጋጅቻለሁ’’ ብለዋል፡፡

በአልን በጋራ ለማክበር እንደ አቅማቸው መዘጋጀታቸውን የሚያስረዱት ወይዘሮ ጸሀይ አለሙ፤ ጎረቤት ለደስታም ሆነ ለሀዘን ደራሽ መሆኑን ለልጆቻቸው በማስተማራቸው በተለይም በበአል ወቅት ከጎረቤት ጋር በአንድነት እንደሚያከብሩ ተናግረዋል፡፡

በሀገሪቱ  የብሄርና ሌሎች ልዩነቶች የሚፈታበት የመቻቻል ባህልን በማጎልበት ለሀገር ሰላምና ደህንነት በጋራ መስራት  እንዳለባቸውም ወይዘሮ ጸሀይ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም