በምስራቅ ጎጃምና በሰሜን ወሎ ዞኖች የአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራ ለማከናወን ዝግጅት ተጠናቋል

137

ደብረ ማርቆስ/ወልዲያ  ታህሳስ 26/2011 በምስራቅ ጎጃምና በሰሜን ወሎ ዞኖች በተያዘው የበጋ ወራት ከ265 ሺህ ሄክታር በሚበልጥ ማሳ ላይ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራ ለማከናወን ዝግጅት መጠናቀቁን የየዞኑ ግብርና መምሪያዎች ገለጹ።    

በምስራቅ ጎጃም ዞን ግብርና መምሪያ የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃልማት ባለሙያ አቶ ጤናው አላምረው ለኢዜአ እንደተናገሩት የአፈር መሸርሸርና የደኖች መራቆትን ለመቀነስ የልማት ሥራው በህብረተሰቡ ተሳትፎ ለማከናወን ዝግጅት ተጠናቋል።

እስካሁንም 870 ተፋሰሶች መለየታቸውንና የልማት ሥራውም ከጥር 15 ቀን 2011 ጀምሮ እንደ የወረዳዎች ፍላጎት እንደሚጀመር አመልክተዋል።

በልማት ሥራው ከ612 ሺህ በላይ አርሶ አደሮች የሚሳተፉ ሲሆን የአፈር እና የውሃ ጥበቃ ሥራውን በተግባር የሚያግዙ 23 ሺህ ቀያሽ አርሶ አደሮችም ሰልጥነዋል፤ አስፈላጊ የልማት መሳሪያዎችም መዘጋጀታቸውን ነው የጠቆሙት።

ስልጠናውን ካገኙ ቀያሽ አርሶ አደሮች መካከል የጎዛምን ወረዳ የአባሊባኖስ ቀበሌ ነዋሪ አርሶአደር የስጋት ዋስይሁን እንዳሉት የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ሥራው የአካባቢን ለምነት በመጠበቅ ምርታማ እንዲሆኑና እንስሳትም መኖ እንዲያገኙ አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑን ተናግረዋል።

በዚህ ዓመት ለሚሰራው የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ሥራ ከባለሙያዎች ጋር በመሆን የመለካት፣ አቅጣጫን የማመለካት እና ሌሎችንም ሥራዎች በፍቃደኝነት ለማከናወን ዝግጅት ማድረጋቸውን ጠቅሰዋል።

የማቻከል ወረዳ የእንቡሊ ቀበሌ ነዋሪ አርሶአደር አነጋግረው ላቀ በበኩላቸው ባለፉት ዓመታት በተሰራው የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ሥራ በአካባቢው ደርቀው የነበሩ ምንጮች መልሰው መፍለቃቸውን ተናግረዋል።

"ዘንድሮም ልማቱ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ያለማንም ቀስቃሽና አስገዳጅነት በራሴ ፍላጎት ልማቱ እንዲጠናከር የበኩሌን እወጣለሁ" ብለዋል።

በተመሳሳይ በሰሜን ወሎ ዞን በዘንድሮው የበጋ ወቅት ከ369 ሺህ በላይ ህዝብ በማሳተፍ በ563 ተፋሰሶች የአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራ ለማከናወን ዝግጅት መደረጉን የገለፁት  በዞኑ ግብርና መምሪያ የአፈርና ውሀ ጥበቃ ባለሙያ አቶ አዲሱ ፈንታው ናቸው።

በእነዚህ ተፋሰሶች 25 ሺህ ሄክታር በሚሸፍን መሬት ላይ የእርከን፣ የክትር፣ የቦረቦር መሬት ማዳንና የእርጥበት ማቆያ ሥራዎች እንደሚከናወኑ ተናግረዋል፡፡

አቶ አዲሱ እንዳሉት ባለፉት ዓመታት በተሰሩ የተፋሰስ ልማት ሥራዎች አካባቢው መልሶ እያገገመና የደን ሽፋኑም እያደገ መጥቷል።

በለሙ ተፋሰሶች ላይ ወጣቶች ተደራጅተው በንብ ማነብና በአትክልትና ፍራፍሬ ልማት ሥራ እንዲሰማሩ መደረጉንም አመልክተዋል።

አርሶ አደሩ በአፈርና ውሀ እቀባ ሥራው የእርከንና ክትር ሥራዎችን ብቻ ሳይሆን የወንዝ ጠለፋ፣ የውሀ ማሰባሰብንና የኮምፖስት ስራዎችንም ጎን ለጎን እንደሚያከናውን ተናግረዋል።

በዞኑ ባለፈው ዓመት 400 ሺህ አርሶ አደር በልማቱ በማሳተፍ 25ሺህ ሄክታር መሬት ላይ የአፈርና ውሀ ጥበቃ ልማት ሥራ መከናወኑን የዞኑን ግብርና መምሪያ መረጃ ያመለክታል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም