ጥምረት እየፈጠሩ ያሉ ፓርቲዎች ከልዩነት ይልቅ በሚያግባባቸው ጉዳይ ላይ መስራት ይኖርባቸዋል

125

አዲስ አበባ ታህሳስ 26/2011 ጥምረት እየፈጠሩ ያሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች ከሀሳብ ልዩነት ይልቅ በሚያግባባቸው ጉዳይ ላይ መስራት እንደሚኖርባቸው ተገለጸ።

በኢትዮጵያ ብዛት ያላቸው የፖለቲካ ፓርቲዎች መኖራቸው ከመንግስት በተጨማሪ ለህብረተሰቡ አማራጭ ሀሳብ ከማቅረብ አንጻርና ጠንካራ ፖለቲካ ፓርቲዎች እንዳይኖሩ አድርጓል የሚሉ ሀሳቦች ይደመጣሉ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ከተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች ጋር ባደረጉት ውይይት ተመሳሳይ ዓላማና የፖለቲካ ርዕዮተ-ዓለም ያላቸው ፓርቲዎች በመዋሃድ ወደ አራት ወይም አምስት የፖለቲካ ፓርቲዎች ከመጡ ድጋፍ እንደሚደረግላቸው ገልጸው ነበር።

ይህን ተከትሎ የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኦዴፓ) ከኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኦዴግ)፤ የአማራ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (አዴፓ) ደግሞ ከአማራ ዴሞክራሲያዊ ኃይሎች ንቅናቄ (አዴኃን) ጋር ውህደት ፈጥረዋል።

ሰማያዊ ፓርቲም ከአርበኞች ግንቦት ሰባት ንቅናቄ፣ ከኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢዴፓ) እንዲሁም አቶ አንዱዓለም አራጌና አቶ ግርማ ሰይፉን ጨምሮ ከቀድሞ የአንድነት ለፍትህና ለዴሞክራሲ ፓርቲ አባላት ጋር ውህደት ለመፍጠር ስምምነት ላይ መድረሳቸው ይታወቃል።

ኢዜአ ይህን አስመልክቶ ያነጋገራቸው በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስና ዓለም አቀፍ ግንኙነት መምህር ተባባሪ ፕሮፌሰር ያዕቆብ አርሳኖ ባለፉት 10 ዓመታት በኢትዮጵያ ፖለቲካ ፓርቲዎች በቁጥርም በአይነትም በከፍተኛ ሁኔታ እንደጨመሩ ያወሳሉ።

ብዙ የፖለቲካ ፓርቲዎች በአገሪቷ መብዛታቸው ጠንካራ ፖለቲካ ፓርቲ እንዳይኖር፣ ህዝቡም የፓርቲዎቹን ዓላማና ራዕይ በግልጽ እንዳይረዳና እንዳያውቅ ማድረጉን ገልጸዋል።

በአሁኑ ወቅት ተመሳሳይ ዓላማ፣ ፍልስፍናና ሀሳብ ያላቸው የፖለቲካ ፓርቲዎች እየተጣመሩ መምጣታቸው ጠንካራ ፓርቲዎች እንዲኖሩ በማድረግ በመንግስት ላይ ተጽእኖ በማሳደር ለአገር ጥቅም በትብብር እንዲሰሩ እንደሚያደርግ ተናግረዋል።

እየተጣመሩ የሚገኙት ፖለቲካ ፓርቲዎች ከሀሳብ ልዩነታቸው ይልቅ በጋራ በሚያግባባቸው ጉዳይ ላይ መስራት እንዳለባቸውና ይህም በህዝቡ ዘንድ ተለይተው እንዲታወቁ እንደሚያደርግ ምሁሩ ይመክራሉ።

የፖለቲካ ፓርቲዎች ተመሳሳይ ሀሳብ እያላቸው በተጠናል ቢሰሩ ራሳቸውን እንደሚያዳክማቸውና አላስፈላጊ ፉክክር እንዲኖር ያደርጋል ያሉት የፖለቲካ ምሁሩ ከዚያም አልፎ እርስ በእርስ እንዲጠላለፉ እንደሚያደርግ ጠቅሰዋል።

ስለዚህም በአገሪቱ ጠንካራና ተወዳዳሪ ፓርቲ ሆኖ ለመውጣት ተመሳሳይ ርእዮተ-ዓለምና መስመር ያላቸው ፓርቲዎች በድርድርና ውይይት ውህደት በመፍጠር በኩል ትኩረት ሊያደርጉ እንደሚገባ ተባባሪ ፕሮፌሰር ያዕቆብ ተናግረዋል።

የፖለቲካ ፓርቲዎች ከምንም በላይ ለህዝብና ለአገር ጥቅም መስራት እንደሚጠበቅባቸውና በዚህም አለመግባባቶችም ሲኖሩ በውይይትና በሀሳብ ክርክር መፍታት እንዳለባቸውም መክረዋል።

የፖለቲካ ፓርቲዎች ተዋህደው ጠንካራ የፖለቲካ ፓርቲ መመስረት ጊዜ የሚፈልግ ጉዳይ መሆኑን ጠቅሰው የአገር እድገትና ብልጽግናን መሰረት አድረገው ከሰሩ የሚያጋጥሟቸውን ፈተናዎች መወጣት እንደሚችሉ አመልክተዋል።

የቀድሞው የሰማያዊ ፓርቲ ሊቀ-መንበር አቶ የሺዋስ አሰፋ ፓርቲያቸው ላለፉት ሁለት ዓመታት በመሰረታዊ ጉዳዮች ላይ ተመሳሳይ ሀሳብ ያላቸው ፓርቲዎች እንዲዋሃዱ ሙከራ ሲያደርግ መቆየቱን ተናግረዋል።

የፖለቲካ ፓርቲዎች ተጣምረው በመስራት ጠንካራና ተወዳዳሪ ፓርቲ እንዳይሆኑ ያደረገው የአስተሳሰብ ልዩነት ሳይሆን የፓርቲዎቹ የባህሪይ ችግርና የአሰራር ስርዓቱ ምቹ ሁኔን ባለመፍጠሩ እንደሆነ አመልክተዋል።

በተለይም የፖለቲካ ፓርቲን ትክክለኛ መስፈርት ያላሟሉ ፓርቲዎች መኖራቸው ህብረተሰቡን ብዥታ ውስጥ እየከተተ መሆኑንና በቀጣይ ልዩ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ አመልክተዋል።

አሁን የመንግስት አቋም ከብዙ ፓርቲዎች ይልቅ በጣት የሚቆጠሩ ጠንካራ ፓርቲዎች እንዲኖሩ መሆኑና ለዚህም ድጋፍ እንደሚያደርግ መግለጹ ያለውን የፖለቲካ ቁርጠኝነት የሚያሳይ ነው ብለዋል።

ተመሳሳይ ዓላማ ያላቸው ፓርቲዎች በመዋሃድ ጠንካራ ፓርቲ መሆንና ከምርጫ ያለፈ ዘለቄታዊ አማራጭ ሀሳብ ለህዝቡ ከማቅረብ ውጪ ምንም አይነት አማራጭ እንደሌለና ፓርቲዎች ለዚህ ተግተው መስራት እንዳባቸውም ተናግረዋል።

የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኦዴፓ) ማዕከላዊ ጽህፈት ቤት የህዝብ አስተያየትና ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ታዬ ደንደአ በበኩላቸው ከኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኦዴግ) ጋር ውህደት የተፈጸመው ፓርቲዎቹ የህዝቡን ተጠቃሚነት በማረጋገጥ ረገድ ተመሳሳይ አቋም ስላለቸው መሆኑን ገልጸዋል።

ሁለቱ ፓርቲዎች የፖለቲካ ፕሮግራማቸውን ሲፈትሹ ዋና ዋና በሚባሉ ጉዳዮች ላይ ልዩነት እንደሌላቸውና ህዝቡ ለሚያነሳው ጥያቄ ምላሽ መስጠት የሚቻለው ጠንካራ ፓርቲ ሲኖርመሆኑን በመገንዘብ ፓርቲዎቹ መዋሃዳቸውን ተናግረዋል።

በአሁኑ ወቅት ህዝቡ በተመሰቃቀለ መንገድ ጥያቄዬን የሚመልስ ፓርቲ አልፈልግም የሚል ሀሳብ እያነሳ በመሆኑ ተመሳሳይ ግብ ያላቸው የተለያዩ ፓርቲዎች ተዋህደው ጠንካራ የፖለቲካ ፓርቲ መሆን ለድርድር የሚቀርብ ጉዳይ አይደለም ብለዋል።

"መደመር" የሚለው እሳቤ በመተባበርና በአንድነት በመስራት ኢትዮጵያን ማሳደግ በመሆኑ ፖለቲካ ፓርቲዎች ተደምረው ጠንካራ ፓርቲ በመሆን ከግል ጥቅም ይልቅ ለአገር እድገት መስራት እንዳለባቸው አመልክተዋል።

የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ለኦሮሞ ህዝብ በትብብር መስራት ከሚፈልጉ ፓርቲዎች ጋር ተወያይቶ በጋራ መስራት እንደሚፈልግ አክለዋል።

በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ህጋዊ እውቅና ያላቸው አገር አቀፍና ክልላዊ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጠቅላላ ቁጥር 62 ሲሆን በመንግስት ጥሪ ተደርጎላቸው ከውጭ የገቡትን ጨምሮ በአጠቃላይ በኢትዮጵያ ከ80 በላይ የፖለቲካ ፓርቲዎች ይገኛሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም