የሪል እስቴት የቤቶች ግንባታ የሚመራበት ሕግ በቅርቡ ወደ ሥራ ይገባል

204

አዲስ አበባ ታህሳስ 26/2011 የሪል እስቴት የቤቶች ግንባታ የሚመራበት የሕግ ማዕቀፍ በቅርቡ ወደ ሥራ ይገባል ተብሎ እንደሚጠበቅ የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር ገለጸ።

የሚኒስቴሩ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ኢትዮጵያ በዴቻ ለኢዜአ እንደተናገሩት፤ በአገሪቱ የሚካሄደው የሪል እስቴት ግንባታ እስካሁን የራሱ የሕግ ማዕቀፍ የለውም።

ይሁንና ዘርፉ በቤቶች ልማት ፖሊሲ ሥር በቤቶች መርሃ-ግብር እንደ አንድ ፓኬጅ ተይዞለት በስትራቴጂ ተደግፎ ለዓመታት ሲተገበር መቆየቱን ነው ያስረዱት።

ዘርፉ እየሰፋ በመምጣቱና ከፍተኛ መዋዕለ-ነዋይ የሚፈስበት መሆኑን በመገንዘብም ከ2005 ዓ.ም ጀምሮ ለሦስት ዓመታት የሕግ ማዕቀፍ ተዘጋጅቷል። 

በተዘጋጀው ረቂቅ ላይ በተለያዩ በአገሪቱ ከተሞች ባለድርሻ አካላትና ኅብረተሰቡ ተወያይቶበት በ2008 ዓም ለውሳኔ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት መላኩን ተናግረዋል።

የሚኒስትሮች ምክር ቤት በረቂቁ ላይ እስካሁን ምንም ምላሽ አለመስጠቱን ገልጸው ረቂቁ በዚህ ዓመት ጸድቆ ወደ ሥራ እንደሚገባ ይጠበቃል ነው ያሉት። 

የሕግ ማዕቀፉም በዋነኝነት የሪል እስቴት ልማትና ግብይትን በተመለከተ በጠራ የሕግ አካሄድ እንዲተገበር በማድረግ የዘርፉን ችግሮች ያስተካክላል ብለዋል።

በተለይም በከተሞች የሚስተዋሉ በመንግሥት፣ በሪል እስቴት አልሚዎችና በተረካቢ የቤት ባለቤቶች በኩል ያሉ አለመግባባቶችንም ያቃልላል ነው ያሉት።

በመሆኑም የሕግ ማዕቀፉ ሥራ ላይ ሲውል እነዚህንና ሌሎችንም ችግሮች በማቃለል ረገድ ሚናው የጎላ መሆኑን ጠቅሰዋል።

መንግሥት ለግል አልሚዎች በሰጠው ፈቃድ መሰረት በአሁኑ ወቅት በርካታ ባለሃብቶች በሪል እስቴት የቤቶች ግንባታ ፕሮጀክት ላይ ተሳታፊ ሆነዋል። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም