ወጣቱ ሀገራዊ ለውጡን ለማስቀጠል አንድነቱን ሊያጎለብት ይገባል...የወጣት ሊግ አመራሮች

74

ባህርዳር ታህሳስ 26/2011 የተጀመረው ሀገራዊ ለውጥ ቀጣይነት እንዲኖረው ወጣቱ ከምንጊዜውም በላይ አንድነቱን በማጎልበት ተባብሮ ሊሰራ እንደሚገባ የኢህአዴግ እህትና አጋር ድርጅቶች የወጣት ሊግ አመራሮች ገለጹ።

የወጣት ሊግ አመራሮቹ በባህር ዳር ከተማ እየተካሄደ ባለው የአማራ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (አዴፓ) ወጣቶች ሊግ 4ኛ መደበኛ ጉባኤ ላይ በተጋባዥነት ተገኝተዋል።

ወጣቶቹ እንደገለጹት በአሁኑ ወቅት ለመጣው ሀገራዊ ለውጥ የኢትዮጵያ ወጣቶች ከአካል ጉዳት እስከ ሕይወት መስዋዕትነት ከፍለዋል።

በአንዳንድ የአገሪቱ አካባቢዎች ለውጡን ለማደናቀፍ የሚደረጉ ጥረቶች መኖራቸውን ጠቁመው፣ በተለይ ወጣቱ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነቱን ለማሳደግ ሀገራዊ ለውጡን አጠናክሮ ማስቀጠል እንዳለበት ተናግረዋል።   

ለእዚህም ከምንጊዜውም በላይ ወጣቱ አንድነቱን በማጎልበት ተባብሮ ሊሰራ እንደሚገባ ነው የገለጹት።

የኦሮሞ ዴሞክራቲክ ፓርቲ (ኦዲፒ) ወጣቶች ሥራ አስፈጻሚ ወጣት ጫላ ኦለቃ እንደገለጸው ወጣቶች ላለፉት ሦስት ዓመታት በሀገሪቱ ሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች እንዲከበሩ፣ የመልካም አስተዳደር ችግሮች እንዲፈቱና ፍታዊ ተጠቃሚነት እንዲኖር ሲጠይቁ እንደነበር አስታውሷል።

በአሁኑ ወቅት በአገሪቱ የተጀመረው ለውጥ እንዲመጣ ወጣቱ ከኢህአዴግ የለውጥ አራማጆች ጋር በመሆን ከፍተኛውን ሚና መጫወቱን አስታውሷል።

"የመጣውን ሀገራዊ ለውጥ ተከትሎም የኢትዮጵያን ህዝብ ሃብት የመዘበሩ፣ ከፍተኛ ሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ የመብት ጥሰት የፈጸሙ ግለሰቦች ተጠያቂ እየሆኑ መጥተዋል" ብሏል።

ይህን ሀገራዊ ለውጥ ለመቀልበስ እየጣሩ ያሉ አካላትን ወጣቱ አንድነቱን አጠናክሮ በጋራ ሊታገለው እንደሚገባም ነው የገለጸው።

አገሪቱን በትክክለኛ የዴሞክራሲ ግንባታ መስመር ለማስገባት እየተሰራ ባለበት በአሁኑ ወቅት ለውጡ እንዲቀለበስ የሚጥሩ አካላት እንዳሉ የተናገረው ደግሞ የደቡብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ዴሞክራሲ ንቅናቄ (ደኢህዴን) ወጣቶች ሊግ ምክትል ሊቀመንበር ወጣት ተስፋዬ ከለቸ ነው።

ወጣት ተስፋዬ እንዳለው ለውጡ እንዲመጣ ምክንያት የሆነው ወጣት አሁንም አንድነቱን በማጠናከር ለውጡን ለማስቀጠል የጎላ አስተዋጽኦ ማድረግ ይኖርበታል።

በህዝቦች መካከል አንድነት በመፍጠር የተጀመረውን አገራዊ ለውጥ ለማስቀጠል በሚያደርገው እንቅስቃሴ የደቡብ  ክልል ወጣት የድርሻውን እንደሚወጣ የበኩሉን እገዛ እንደሚያደርግ አስረድቷል።

የቤንሻንጉል ጉምዝ ዴሞክራሲ ፓርቲ (ቤጉዴፓ) ወጣቶች ሊግ ምክትል ሊቀመንበር ወጣት ሀብታሙ ውባልታ በበኩሉ በኢትዮጵያ ህዝቦች መካከል እርስ በእርስ መቃቃር እንዲፈጠር የሚሯሯጡ ኃይሎችን ወጣቱ መታገል እንዳለበት ተናግሯል።

የአካባቢውን ሰላም በማስጠበቅና ብሄርን ከብሄር በማጋጨት ስራ ላይ የተጠመዱ አካላትን ሴራ በማክሸፍ ለመንግስት ያለውን ወገናዊነት እንዲያረጋግጥም መልክቱን አስተላልፏል።

እርስ በእርስ ተጋብቶና ተዋልዶ ለዘመናት አብሮ የኖረውን የኢትዮጵያ ህዝብ ለመለያየትና ወደግጭት እንዲገባ የሚደረገውን ጥረት ወጣቱ ህብረተሰብ  ሊያስቆመው እንደሚገባም አመልክቷል።

በተለይ የአማራና የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ወጣቶች ከምንጊዜውም በላይ ራሳቸውን የጥፋት ኃይሎች መጠቀሚያ ከመሆን በመከላከል ለዘላቂ ሰላም እንዲሰሩ ጠይቋል።

የወጣት ሊግ አመራሮቹ የአማራ ዴሞክራሲ ፓርቲ (አዴፓ) ወጣቶች ሊግ ለሚወስናቸው ውሳኔዎች ተፈጻሚነት ከጎኑ እንደሚቆሙም ቃል ገብተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም