በጎንደር ከተማ የተጀመረው ዞናል ሆስፒታል ግንባታ መቋረጡ ቅሬታ እንደፈጠረባቸው ነዋሪዎች ገለፁ

91

ጎንደር ታህሳስ 26/2011 በጎንደር ከተማ የተጀመረው የአይራ ዞናል ሆስፒታል ግንባታ መቋረጡ ቅሬታ እንደፈጠረባቸው ነዋሪዎች ገለፁ፡፡

የማእከላዊ ጎንደር ዞን ጤና መምሪያ በበኩሉ የዞናል ሆስፒታሉ ግንባታ አለመጠናቀቅ በገጠር ሆስፒታሎች የህክምና አገልግሎት አሰጣጥ ላይ ጫና ፈጥሯል፡፡

የጎንደር ዩኒቨርሲቲ አጠቃላይ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል በበኩሉ የአይራ ዞናል ሆስፒታል የሪፈራል ስርአቱን በማጠናከር ለቀላል ህክምና ወደ ሆስፒታሉ በየእለቱ የሚመጡ ታካሚዎችን ችግር በወቅቱ ለመፍታት ያስችል ነበር ብሏል፡፡

በከተማው የአዘዞ ከተማ ነዋሪ አቶ አለምነው ታደሰ እንደተናገሩት መንግስት ከፍተኛ በጀት መድቦ ያስጀመረው የአይራ ዞናል ሆስፒታል ግንባታው ሊጠናቀቅ ሲቃረብ መቋረጡ ቅሬታ ፈጥሮባቸዋል፡፡

የሆስፒታሉ ግንባታ ተጠናቆ አገልግሎት ባለመጀመሩ ለከፍተኛ ህክምና በአካባቢው ብቸኛ ወደ ሆነው ጎንደር ዩኒቨርሲቲ ሆስፒታል በመሄድ በወረፋ መብዛት መጉላላት እየደረሰባቸው መሆኑን ገልፀዋል፡፡

ሌላው የአዘዞ ከተማ ነዋሪ አቶ መልሰው ታምሩ በበኩላቸው ''ሆስፒታሉ ለአዘዞ ቅርብ እንደመሆኑ ወላጆችም ሆነ ታማሚዎች በአቅራቢቸው የህክምና አገልግሎት እንዲያገኙ እገዛው የላቀ ነበር''  ብለዋል፡፡

''የሆስፒታል ግንባታ በጅምር መቅረቱ ቅሬታ ፈጥሮብኛል'' ያሉት ደግሞ ወይዘሮ መልሽው በላይ የተባሉ የአይራ ቀበሌ ነዋሪ ናቸው፡፡

ሆስፒታል ከፍተኛ ወጪ ከወጣበት በኋላ በጅምር መቅረቱ አግባብነት የሌለው በመሆኑ በአፋጣኝ ግንባታው እንዲጀመር ነዋሪዎቹ ጠይቀዋል፡፡

የማእከላዊ ጎንደር ዞን ጤና መምሪያ ምክትል ኃላፊ አቶ ደስታው ክብረት በበኩላቸው በክልሉ ጤና ቢሮ በኩል በ2005 ዓ.ም ግንባታው በ168 ሚሊዮን ብር የተጀመረው የአይራ ዞናል ሆስፒታል በውሉ መሰረት መጠናቀቅ የነበረበት በ2007 ነው፡፡

ግንባታው 83 በመቶ ከደረሰ በኋላ መቋረጡን የገለጹት ምክትል ኃላፊው በወቅቱ እዲጠናቀቅ ቢደረግ በዞኑ የተለያዩ ወረዳዎች ስራ የጀመሩ የገጠር ሆስፒታሎች የሚልኳቸውን ታካሚዎች በመቀበል ማስተናገድ ይችል ነበር፡፡

መምሪያው ግንባታውን የመቆጣጠርና የመከታተል ውክልና ባይኖረውም ከፍተኛ ወጪ የወጣበት ፕሮጀክት በወቅቱ ተጠናቆ ለህዝብ አገልግሎት እንዲሰጥ ለክልሉ ጤና ቢሮ በተደጋጋሚ ማሳወቁን ገልጸዋል፡፡

የጎንደር ዩኒቨርሲቲ አጠቃላይ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ዋና ስራ አስፈጻሚ ዶክተር ሲሳይ ይፍሩ በበኩላቸው ዞናል ሆስፒታሉ በዩኒቨርሲቲ ሆስፒታሉ የሚታየውን የታካሚዎች መበራከትና የህክምና አገልግሎት ጫና ለመቀነስ ያግዝል የሚል ተስፋ እንደነበራቸው ተናግረዋል፡፡

ዩኒቨርሲቲ ሆስፒታሉ የዞናል ሆስፒታሉን ቀሪ ግንባታ በማጠናቀቅ ለህክምና ተማሪዎች የተግባር ትምህርት መስጫና ለዞኑ ህዝብም የህክምና አገልግሎት ተደራሽ ለማድረግ እንዲቻል ጥያቄ ቢያቀርብም በሚመለከታቸው አካላት አጥጋቢ ምላሽ እንዳልተሰጠው አስታውቀዋል፡፡

የሆስፒታሉ ግንባታ የተጓተተው በተቋራጩ የአቅም ውስንነት ምክንያት ነው፤ ችግሩን ለመፍታት የክልሉ ርዕሰ መስተዳደር ጭምር ጥረት ቢያደርጉም እስካሁን መፍታት አልተቻለም ያሉት ደግሞ የክልሉ ጤና ጥበቃ ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ክንዲሁን አግዘው ናቸው።

ግንባታው ከፍተኛ መጓተት አለበት እንጂ ሙሉ በሙሉ ተቋርጧል የሚለው መረጃ የተሳሳተ መሆኑን ጠቅሰው፤ ባለፈው ክረምት ከተቋራጩ ጋር በተደረገ ውይይት እስከ ታህሳስ ወር 2011 መጨረሻ አጠናቆ እንዲያስረክብ እድል የተሰጠው ቢሆንም ከችግሩ መላቀቅ አልቻለም።

ግንባታ በመጓተቱ ወጭው ወደ 180 ሚሊዮን ከፍ ብሏል ያሉት ምክትል ኃላፊው አሁን ላይ የግንባታው 85 በመቶ መጠናቀቁን ገልፀዋል።

በመሆኑም አብዛኞቹ የማጠናቀቂያ የግንባታ ቁሳቁሶች ተገዝተው የቀረቡ በመሆናቸው ከቻለ ተቋራጩ ተጨማሪ እድል ተሰጥቶት እንዲጨርስ ካልቻለ ግን ለሌላ ተቋራጭ በመስጠት እስከ ዓመቱ መጨረሻ በማጠናቀቅ ስራ እንደሚጀምር ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም