በአሶሳ ከተማ የግል ክሊኒኮች ሌሊት አገልግሎት ስለማይሰጡ ተቸግረናል – ነዋሪዎች

811

አሶሳ ታህሳስ 26/2011 በአሶሳ ከተማ የሚገኙ የግል ክሊኒኮች አብዛኛዎቹ በምሽት አገልግሎት ባለመስጠታቸው መቸገራቸውን አስያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ ነዋሪዎች ተናገሩ፡፡

የከተማ አስተዳደሩ የጤና ጥበቃ መምሪያ በበኩሉ በግል ክሊኒኮች አገልግሎት መስጫ ሰአት ዙሪያ ከነዋሪዎች የተነሳው ቅሬታ ትክክል መሆኑን በመቀበል ችግሩን ለማስተካከል እንደሚሰራ አስታውቋል፡፡

ወይዘሪት ሜሮን መላኩ ”በከተማዋ የሚገኙ ክሊኒኮች ለ24 ሰዓት እንደሚሰሩ የሚገልፅ ማስታወቂያ ቢያስቀምጡም ከምሽቱ አራት ሰዓት ካለፈ አገልግሎት መስጠት ያቆማሉ” ብላለች፡፡

ከሳምንት በፊት እናቷ በድንገት በመታመማቸው በአቅራቢያዋ የሚገኙ የግል ክሊኒኮች በምሽት ብትሄድም ዝግ በመሆናቸው አገልግሎት ማግኘት እንዳልቻለች አስታውሳለች፡፡

ሌላ የከተማዋ ነዋሪ የሆኑት ወይዘሮ እፀገነት በቀለ አብዛኛዎቹ የግል ክሊኒኮች ምሽት ላይ ብቻ ሳይሆን እሁድ ቀንም እንደሚዘጉ መታዘባቸውን ገልፀዋል፡፡

የህክምና አገልግሎት እንደሌሎች የስራ ዘርፎች ባለመሆኑ የሚመለከተው አካል ቁጥጥር ሊያደርግ እንደሚገባም ጠቁመዋል፡፡

አቶ ደጀኔ ደምሴ የተባሉ የከተማዋ ነዋሪ በሰጡት አስተያየት በከተማዋ የሚገኙ አብዛኛዎቹ የግል ክሊኒኮች ከምሽት በኋላ ዝግ እንደሚሆኑ መታዘባቸውን ተናግረዋል፡፡

በከተማ አስተዳደሩ የሚደረገው ክትትል አናሳ መሆን ችግሩን እንደፈጠረው እንደሚያምኑም ገልፀዋል፡፡

ኢዜአ ባልደረባ ባደረገው ምልከታም አብዛኛዎቹ የግል ክሊኒኮች ምሽት ላይ አግልግሎት መስጠት እንደሚያቆሙ አረጋግጧል፡፡

በክልሉ የግል ጤና ተቋማት ማህበር ፕሬዝዳንት አቶ ምትኩ በቀለ ”የግል ክሊኒኮቹ የ24 ሰዓት አገልግሎት የመስጠት ግዴታ የለባቸውም” ብለዋል፡፡

ስህተቱ አንዳንድ ክሊኒኮች ለ24 ሰዓት አገልግሎት እንደሚሰጡ በማስታወቂያ መግለፃቸው እንደሆነ ገልፀዋል፡፡

የከተማ አስተዳደሩ የጤና መምሪያ ጤናና ጤና ነክ አገልግሎት ዋና ስራ ሂደት ባለቤት አቶ በቀለ ዘሪሁን በበኩላቸው ከነዋሪዎች የተነሳው ቅሬታ ትክክለኛ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

”በከተማዋ የሚገኙ የግል መካከለኛ ክሊኒኮች 24 ሰዓት አገልግሎት የመስጠት ግዴታ አለባቸው” ብለዋል፡፡

የጤና መምሪያ ካለበት የሰው ኃይል እጥረት አንፃር የቁጥጥር ስራውን በብቃት መፈፅም እንዳልቻለ ጠቁመዋል፡፡

በቀጣይ ከክሊኒኮቹ አገልግሎት አሰጣጥ ችግሮቻቸውን እንዲያስተካክሉ ውይይት በማድረግ ወደ እርምጃ እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡

በከተማዋ አስር መካከለኛ ክሊኒኮች አገልግሎት በመስጠት ላይ እንደሚገኙ የከተማ አስተዳደሩ ጤና ጥበቃ መምሪያ መረጃ ያመላክታል፡፡