የኢትዮጵያ እጅ ኳስ ፕሪሚየር ሊግ ነገ በሚካሄዱ ጨዋታዎች ይጀመራል

78

አዲስ አበባ ታህሳስ 26/2011 የ2011 ዓ.ም የኢትዮጵያ እጅ ኳስ ፕሪሚየር ሊግ ነገ በአዲስ አበባና በክልል ከተሞች በሚካሄዱ ጨዋታዎች ይጀመራል።

"የሊጉ ውድድር ታህሳስ 6 ቀን 2011 ዓ.ም ይጀመራል" ቢባልም በክለቦች ምዝገባና በሌሎች ምክንያቶች ሳይጀመር ቆይቷል።

አስር ክለቦች በሚሳተፉበት የፕሪሚየር ሊጉ ውድድር ጎንደር ከተማ የዘንድሮው ውድድር ዓመት አዲስ ተሳታፊ ክለብ ነው።

ነገ በአዲስ አበባ ትንሿ ስታዲየም ኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ ከፌዴራል ማረሚያ ቤቶች ከጠዋቱ ሶስት ሰዓት፣ ፌዴራል ፖሊስ ከመቐለ ሰብዓ እንደርታ ከረፋዱ 4 ሰዓት ከ30 ደቂቃ ላይ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።

በክልል ከተሞች ዱራሜ ላይ ከምባታ ዱራሜ ከመከላከያ፣ ድሬዳዋ ላይ ድሬዳዋ ከተማ ከሊጉ አዲስ ተሳታፊ ክለብ ጎንደር ከተማ ጋር በተመሳሳይ ሶስት ሰዓት ላይ ይጫወታሉ።

ከነገ በስቲያ የአምናው የፕሪሚየር ሊግ አሸናፊ ቂርቆስ ክፍለ ከተማ ወደ ቡታጅራ በማቅናት ከቡታጅራ ከተማ ጋር ከጠዋቱ ሶስት ሰዓት ላይ ጨዋታውን ያደርጋል።

የኢትዮጵያ እጅ ኳስ ፌዴሬሽን ህዳር 8 ቀን 2011 ዓ.ም ባደረገው ጠቅላላ ጉባኤ የባለፈው በእጅ ኳስ ፕሪሚየር ሊግ የታዩ የስፖርታዊ ጨዋነት ችግሮች ዳግም እንዳይከሰቱ መስራት እንዳለባቸው የጉባኤው አባላት መግለጻቸው የሚታወስ ነው።

ብሔራዊ ፌዴሬሽኑም የስፖርታዊ ጨዋነት ጉድለቶችን ለማስወገድ ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት እያደረገ መሆኑን የኢትዮጵያ እጅ ኳስ ፌዴሬሽን ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት በላከው የጽሁፍ መግለጫ አስታውቋል።

የ2011 ዓ.ም የኢትዮጵያ እጅ ኳስ ፕሪሚየር ሊግ ሶስተኛው የውድድር ዓመቱ ነው።

ፕሪሚየር ሊጉ ከ2009 ዓ.ም ጀምሮ በመካሄድ ላይ ሲሆን፤ መከላከያ በ2009 ዓ.ም እና ቂርቆስ ክፍለ ከተማ  የባለፈው ዓመት የሊጉ አሸናፊ መሆናቸው ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም