የአመራር ቁርጠኝነት ማነስ ጥራት ያለው አገልግሎት ህብረተሰቡ እንዳያገኝ እያደረገ ነው፡- ጤና ሚኒስቴር

837

ባህር ዳር ታህሳስ 26/2011 በሆስፒታል አመራር ቁርጠኝነት ማነስ ለህብረተሰቡ እየተሰጠ ያለው የጤና አገልግሎት ጥራት በአማካኝ በ50 በመቶ ብቻ መሆኑን የኢፌድሪ ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር አስታወቀ።

በሃገሪቱ በዓመት እየተሰጠ ያለው የቀዶ ሕክምና አገልግሎትም ከአምስት በመቶ እንደማይበልጥ ተጠቁሟል።

የሆስፒታሎች የበጀት ዓመቱ ግማሽ ዓመት ዕቅድ አፈጻጸም ግምገማ በባህር ዳር ከተማ እየተካሄደ ነው።

የጤና ጥበቃ ሚኒስትሩ ዶክተር አሚር አማን በእዚህ ወቅት እንዳስታወቁት በ2011 ግማሽ በጀት ዓመት በ50 ሆስፒታሎች ላይ በተካሄደ የአገልግሎት ጥራት ግምገማ ዝቅተኛ ሆኖ ተገኝቷል።

በሆስፒታሎቹ በ197 የአገልግሎት ጥራት መገምገሚያ መስፈርቶች በተካሄደ ዳሰሳ ዝቅተኛው 11 ከመቶ ከፍተኛው ደግሞ 88 ከመቶ ሆኖ መገኘቱን ተናግረዋል።

በተለይም የተሻለ ግብዓትም ሆነ የሰው ኃይል የሚገኝባቸው የዩኒቨርሲቲ ሆስፒታሎች የአገልግሎት ጥራታቸው 46 ከመቶ፤ በአንጻሩ የክልል ሆስፒታሎች 52 ከመቶ ሆኖ መገኘቱን ዶክተር አሚን ገልጸዋል።

የህክምና መሳሪያዎች አለመሟላት፣ የመድኃኒት አቅርቦትና የቤተሙከራ ግብዓቶች እጥረት ያልተፈቱ ችግሮች ቢሆኑም ባለው አቅርቦት ልክ ለህክምና የመጣውን ታማሚ ለመርዳት በቁርጠኝነት አለመስራት ግን ዋናው ምክንያት መሆኑን አስረድተዋል።

“በተለይም በሆስፒታሎች ተቀራራቢ የግብአት አቅርቦትና እጥረት እያለ የአፈጻጸም ልዩነት መኖሩ የአመራሩ ቁርጠኝነት ማነስ ነው” ብለዋል።

በቀጣይ በመንግስት በኩል የሚስተዋሉ የሕክምና መሳሪያዎችንም ሆነ የመድኃኒት አቅርቦት እጥረቶችን በመፍታት ከደረጃ በታች የሚሰሩ ተቋማትን የማስተካከል ሥራ አንደሚከናወን አመልክተዋል።

“በዓለም አቀፍ መለኪያ መሰረት እስከ 100 ሚሊዮን የህዝብ ቁጥር ያላቸው ሃገራት በዓመት ቁጥራቸው ከአምስት ሚሊዮን ለማያንስ ታማሚዎች የቀዶ ሕክምና ይሰጣሉ” ያሉት ደግሞ በሚኒስትሩ የህክምና አገልግሎት ዳይሬክተር ጀኔራል ዶክተር ዳንኤል ገብረሚካኤል ናቸው።

በኢትዮጵያ በዓመት የቀዶ ሕክምና የሚያገኙት ህሙማን ቁጥር 250 ሺህ ወይም ከአምስት በመቶ እንደማይበልጥ ገልጸው፣ ለእዚህም ታመው ወደህክምና ተቋማት የሚመጡ ህሙማን በተለያየ ምክንያት በወቅቱ ሕክምና አለማግኘታቸው መሆኑን አስረድተዋል።

በተለይም በሁሉም የጤና ተቋማት የቀዶ ሕክምና ክፍል አለመኖር፣ የባለሙያ እጥረት አለመፈታት፣ የህምና ግብዓት አለመሟላት፣ የህክምና ተቋማት ተደራሽ አለመሆን ለችግሩ አስተዋጽኦ ማድረጋቸውን ተናግረዋል።

ለአብነትም በአሁኑ ወቅት ከ8 ሺህ በላይ ህሙማን ከ6 ወር እስከ ሁለት ዓመት የቀዶ ሕክምና ቀጠሮ ይዘው እየተጠባበቁ መሆናቸውን ጠቅሰዋል።

ችግሩን በጊዜያዊነት ለመፍታት ሕሙማን የቀዶ ሕክምና በዘመቻ እንዲያገኙ ጥረት እየተደረገ ሲሆን በዘላቂነት ለመፍታትም በተመረጡ 410 ጤና ጣቢያዎች የቀዶ ሕክምና ክፍል በመገንባት ላይ መሆኑን ተናግረዋል።

“በቀጣይም ባለሙያዎችን በማሰልጠንና የተለዩ የግብዓት ችግሮችን ተደራሽ በማድረግ አገልግሎቱን የሚያገኙ ህሙማንን ቁጥር በዓመት ወደ 500 ሺህ ከፍ ለማድረግ ግብ ተጥሎ እየተሰራ ይገኛል” ብለዋል።

እንደ ዶክተር ዳንኤል ገለጻ የሆስፒታሎችን የጥራት መጓደል ለማስተካከል የተለዩ ችግሮችን በመፍታት ጥራቱን አሁን ካለበት 50 በመቶ ወደ 80 በመቶ ለማድረስ ታቅዷል።

የአማራ ክልል ጤና ቢሮ ኃላፊ ዶክተር አበባው ገበየሁ በበኩላቸው እንዳሉት በአሁኑ ወቅት ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች በፍጥነት እየተዛመቱና ህብረተሰቡን እየጎዱት ነው።

ዶክተር አበባው እንዳሉት የበሽታዎችን የስርጭት ፍጥነትና የማህበረሰቡን የግንዛቤ ደረጃ የሚመጥን ቀልጣፋና ጥራት ያለው አገልግሎት በሆስፒታሎች ያለመስጠት ችግር ይስተዋላል።

“በተለይም የግብዓት አቅርቦት ክፍተት፣ የሰው ኃይል አለመሟላት፣ የመሰረተ ልማት ችግርና የአገልግሎት አሰጣጥ መጓደል ህብረተሰቡ በጤና ተቋማት እምነት እንዳያገኝ እያደረገው ነው” ብለዋል።

በመሆኑም ችግሩን ለመፍታት በተደራጀ አግባብ መስራት ይገባል ያሉት ዶክተር አበባው በቀጣይ ለጥራት መጓደል ምክንያት የሆኑ ችግሮችን በመፍታት የተሻለ አገልግሎት ለመስጠት እንደሚሰራ አመልክተዋል።

ሃገር አቀፍ የሆስፒታሎች የግማሽ ዓመት አፈጻጸም ግምገማ እስከ ነገ የሚቆይ ሲሆን የስፒታል አመራሮችና የሚመለከታቸው አካላት ተሳታፊ መሆናቸው ታውቋል።