በእውቀት ላይ ተመስርቶ ሞጋች ለመሆን ወጣቱ የንባብ ልምዱን ማዳበር እንዳለበት ተጠቆመ

68

ደሴ ታህሳስ 25/2011 በእውቀት ላይ ተመስርቶ   ሞጋች ለመሆን ወጣቱ የማንበብ ልምዱን ሊያዳብር እንደሚገባ ተጠቆመ፡፡

"ማንበብ ሙሉ ሰው ያደርጋል" በሚል መሪ ሀሳብ እስከ ነገ የሚቆይ የንባብ ሳምንት በደሴ ከተማ ተጀምሯል፡፡

በዚህ ስነስርዓት ወቅት የከተማዋ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አቶ ተስፋዬ ጫኔ  እንዳሉት  ወጣቱ በማንኛውንም ጉዳይ ላይ ምክንያታዊ ለመሆን የማንበብ ልምዱን ሊያዳበር ይገባል፡፡

"አሳሳች ማህበራዊ ሚዲያዎች በበዙበት ወቅት የተለያዩ መጽሐፍት  በማንበብ የኢትዮጵያን ታሪክ፣ ወግና ባህል ካልተረዳን በተሳሳተ መረጃ ወደ ጥፋት ልናመራ እንችላለን" ብለዋል፡፡

በእውቀት ላይ ተመስርቶ   ሞጋች ለመሆን ፣ በራሱ የተማመነና ምክንያታዊ ትውልድ ለመቅረጽ ንባብ ጉልህ ሚና እንዳለውና ይህን ማዳበር እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡

የብሄራዊ ቤተ-መጽሀፍትና ቤተ-መዛግብት ኤጀንሲ መድረክ ዝግጅትና ህትመት ቡድን መሪ አቶ ዳንኤል ለሜ "በትኩረት ማንበብና እንድምታው" በሚል ርዕስ ጥናታዊ ጽሁፍ አቅርበዋል፡፡

በዚሁ ጽሁፋቸው " ትውልዱ በመጤ ባህልና ሱስ ተጠምዶ ኢትዮጵያዊ ማንነቱን እንዳይረሳ በየቀኑ ማንበብ ይጠበቅበታል "ብለዋል፡፡

ጀማሪ አንባቢ በየቀኑ 15 ደቂቃ  ጠቃሚ መጽሐፍትን መርጦ በማንበብ በየጊዜዉ አቅሙን ማሳደግ እንደሚችል በጥናታዊ ጽሁፉ አመላክተዋል፡፡

በክብር እንግድነት የተገኙት ደራሲ ኃይለ መለኮት መዋዕል በሰጡት አስተያየት  አዳዲስ ሀሳቦችን ለማፍለቅ፣ ተረጋግቶ ለማሰብ፣ ውሳኔ ለማስተላለፍና ለቤተሰባዊና ሀገራዊ ጉዳዮች ንባብ ወሳኝ መሆኑን ገልጸው ልምዳቸውንም አካፍለዋል፡፡

አቶ መሃመድ አሊ የተባሉት የአካባቢው ነዋሪ በበኩላቸው  በከተማው መጽሀፍት ቤቶች ማስፋፋት እንደሚገባ አመልክተዋል፡፡

በንባብ ሳምንቱ የሚነበቡ የተለያዩ መጽሐፍት፣ የባህል ምሽት፤ የንባብ ውድድርና ሌሎችም አስተማሪ ዝግጅቶች በወሎ ዩኒቨርሲቲ መዘጋጀቱ ተገልጿል፡፡

በንባብ ሳምንቱ ማስጀመሪያ ስነሰርዓት  ከከተማው የተወጣጡ ወጣቶች፣ ተማሪዎችና ሌሎችም የህብረተሰብ ክፍሎች ተሳትፈዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም