በማዕከላዊ ጎንደር ነጭ ሽንብራ አምራቾች የገበያ ችግር እንደገጠማቸው ተናገሩ

70

ጎንደር ታህሳስ 25/2011 በገበያ እጦት ለኪሳራ እየተዳረጉ መሆናቸውን በማዕከላዊ ጎንደር ዞን ነጭ ሽንብራ አምራች አርሶ አደሮች ተናገሩ፡፡

ጸሃይ የገበሬዎች ህብረት ስራ ዩንየን በበኩሉ የአርሶአደሮችን የገበያ ችግር ለመፍታት 20ሺ ኩንታል ሽንብራ ከአርሶ አደሩ በመረከብ ለውጪ ገበያ ለመላክ አቅዷል፡፡

የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ዘንድሮ ሽንብራና አኩሪ አተርን ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ግብይት ስርአት እንዲገባ ማድረጉን አስታውቋል፡፡

በዞኑ የጣቁሳ ወረዳ  አርሶአደር አባይ ምስክር "ላለፉት አራት ዓመታት ነጭ ሽንብራን ባመርትም ገበያ በማጣት ለቤት ውስጥ ፍጆታ ለማዋል ተገድጃለሁ "ሲሉ ለኢዜአ ተናግረዋል፡፡

ነጭ ሽንብራ ከቀይ ሽንብራ በምርታማነቱ ቢሻልም  በሀገር ውስጥ ገበያ ተፈላጊነቱ ዝቅተኛ በመሆኑ አምና ያመረቱት  አምስት ኩንታል ሽንብራ በጎተራ ተቀምጦ ለነቀዝ መጋለጡን አመልክተዋል፡፡

ሌላው የዚሁ ወረዳ  አርሶአደር ባይለየኝ ጥፍጡ በበኩላቸው "ግብርና ምርምር ያቀረበልኝን የነጭ ሽንብራ ዝርያ ላለፉት ሁለት ዓመታት አምርቼ ለገበያ ባቀርብም ገዥ በማጣት ለኪሳራ ተዳርጌያለሁ" ብለዋል፡፡

አምና ከሩብ ሄክታር ያገኘትን ስድስት  ኩንታል ነጭ ሽንብራ ቀይ ሽንብራ ለኩንታል ከሚሸጥበት 2ሺህ ብር ባነሰ ዋጋ በ1ሺ 500 ብር ሂሳብ በኪሳራ ለመሸጥ መገደዳቸውን ተናግረዋል፡፡

" ምርቱ በውጪ  ገበያ አዋጪነት  ያለው በመሆኑ  የሽንብራ ምርታችንን ተረክቦ ለውጪ ገበያ የሚያቀርብልን አካል እንፈልጋለን "ያሉት ደግሞ የምዕራብ ደንቢያ ወረዳ  አርሶአደር አቸነፍ ገበያው ናቸው፡፡

ነጭ ሽንብራ እንዲያመርቱ  ከምርጥ ዘር አቅርቦት ጀምሮ አዳዲስ የግብርና አሰራሮችን  እንዲጠቀሙ ድጋፍ ያደረጉላቸው አካላት ገበያ በማፈላለግ ጭምር እንዲያግዟቸው  አርሶአደሮቹ ጠይቀዋል፡፡

በጎንደር ከተማ የሚገኘው የጸሃይ የገበሬዎች ህብረት ስራ ዩንየን ስራ አስኪያጅ አቶ እንዳልክ አቤ በበኩላቸው የነጭ ሽንብራ አምራች አርሶአደሮችን የገበያ ችግር ለመፍታት ዩንየኑ ገበያ የማፈላለግ ስራ እያከናወነ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ዩንየኑ ዘንድሮ ከ20ሺ ኩንታል በላይ ነጭ ሽንብራ ከአርሶአደሩ በመረከብ በኢትዮጵያ ምርት ገበያ በኩል ለህንድ ገበያ ለማቅረብ አቅዶ እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በኢትዮጵያ ምርት ገበያ የግብይትና የመጋዘን አገልግሎት ደህንነትና ቁጥጥር የስራ ክፍል ኃላፊ አቶ በረከት መሰረት ምርት ገበያው በያዝነው ወር ሽንብራና አኩሪ አተርን ለአለም ገበያ የሚቀርብበትን የግብይት ስርዓት መጀመሩን አስታውቀዋል፡፡

በማዕከላዊ ጎንደር ጣቁሳን ጨምሮ በ6 ወረዳዎች በየዓመቱ ከ50ሺ ሄክታር በላይ መሬት አርሶ አደሩ ሽንብራን በስፋት ያለማል፡፡

በ2010/11 የምርት ዘመን በሽንብራ ከለማው መሬት ከ900ሺ ኩንታል ምርት እንደሚጠበቅ በዞኑ ግብርና መምሪያ የሰብል ባለሙያ የሆኑት ወይዘሮ እንኩዋየሁሽ ሙሉ ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም