የእንቦጭ አረም ከ2 ሺህ ሄክታር በሚበልጥ የአባያ ሐይቅ ላይ መስፋፋቱ ተጠቆመ

1221

አርባምንጭ ታህሳስ 25/2011 በአባያ ሐይቅ የተከሰተው እንቦጭ አረም ከ2 ሺህ ሄክታር በሚበልጥ የሐይቁን ክፍል ላይ መስፋፋቱን የጋሞ ዞን አካባቢ ጥበቃና ደን ጽህፈት ቤት አስታወቀ፡፡

ከመጪው ጥር ወር አጋማሽ ጀምሮ የተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎችን በማሳተፍ አረሙን በዘመቻ የመንቀል ሥራ እንደሚከናወንም ተመልክቷል።

የጽህፈት ቤቱ ኃላፊ አቶ ጋንቡራ ጋንታ ለኢዜአ እንደተናገሩት በአባያ ሐይቅ ላይ በ2009 ዓ.ም የተከሰተው የእንቦጭ አረም እየተስፋፋ መጥቶ በአሁኑ ወቅት ከ2 ሺህ ሄክታር በላይ የሐይቁን ክፍል ሸፍኗል ፡፡

ከእዚህ በተጨማሪ አረሙ በሐይቁ ዙሪያ የሚገኙ የተለያዩ የእጽዋት ዝርያዎችን በማጥፋት በሐይቁ ስነ-ምህዳር ላይ ከፍተኛ ጉዳት እያስከተለ መሆኑን አስረድተዋል ፡፡

እንደኃላፊው ገለጻ አረሙ በሐይቁ ውስጥ በቂ የፀሐይ ብርሃን እንዳይገባ ማድረጉ በውሃው ውስጥ ባሉ የእንስሳት ዝርያዎች ላይ ጉዳት እየደረሰ ነው፡፡

የእንቦጭ አረሙ መርዛማ ንጥረ ነገር የያዘ በመሆኑ የተመገቡት በርካታ የቤትና የዱር እንስሳት እየሞቱና በበብዝሃ ህይወት ላይ ዘርፈ ብዙ ችግር እያስከተለ መሆኑንም አስረድተዋል፡፡

ሐይቁን ለመታደግ ከአርባ ምንጭ ዙሪያና ከምዕራብ አባያ ወረዳዎች ከ10 ሺህ በላይ የህብረተሰብ ክፍሎችን በማሳተፍ 36 ሄክታር ላይ የነበረውን ማስወገድ ቢቻልም አገራዊ ለውጡን ተከትሎ በተፈጠረው አለመግባባት ሥራው መቋረጡን አቶ ጋንቡራ ገልጸዋል፡፡

“ሐይቁን ከእንቦጭ አረም በጊዜ መከላከል ካልተቻለ ላለመጥፋቱ ዋስትና የለውም”ያሉት ኃላፊው ከጥር ወር አጋማሽ ጀምሮ ለ4 ወራት የሚቆይ አረም የማስወገድ ዘመቻ እንደሚካሄድ ተናግረዋል ፡፡

አረሙን ለማስወገድ ማሽን እንደማያስፈልግ ጠቁመው፣ በዘመቻው መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችን ጨምሮ ከአርባ ምንጭ ከተማ ፣ ከአርባ ምንጭ ዙሪያና ከምዕራብ ዓባያ ወረዳዎች የሚመጡ የህብረተሰብ ክፍሎች እንደሚሳተፉ አስታውቀዋል፡፡

በምዕራብ ዓባያ አልጌ ቀበሌ የ ”ሰላም ዓሣ አስጋሪዎች ማህበር” ፀሐፊ ወጣት መጎስ መኮንን አረሙ በአጭር ጊዜ ውስጥ በፍጥነት የውሃውን አካል እየሸፈነ ስለመምጣቱ መታዘቡን ለኢዜአ ገልጿል፡፡

“ይህም በዓሣ ምርት ላይ ጉዳት ከማስከተሉም በላይ ሐይቁን መሰረት አድርገው የሚተዳደሩ የህብረተሰብ ክፍሎችን ስጋት ውስጥ እየጣለ ነዉ” ብሏል ፡፡

” አረሙ እርስ በርስ ተጠላልፎ ሣር እንዳይበቅል በማድረጉ በሐይቁ አቅራቢያ ለከብቶች መኖ ሣር እየጠፋ ነው ” ያሉት ደግሞ በአርባ ምንጭ ዙሪያ ወረዳ የጫኖ ሚሌ ቀበሌ አርሶ አደር ባበና ዛዋ ናቸው፡፡

በዚህ ምክንያት እንቦጩን የሚመገቡ እንስሳት እየሞቱና ህልውናችን አደጋ ላይ እየወደቀ መምጣቱን አስረድተዋል፡፡

መንግስታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች መካከል “ የአኪያ ማልቲ ሚዲያ ” አስተባባሪ ወጣት ፋሪስ ንጉሤ በበኩሉ የአባያ ሐይቅ የሃገር ሀብት በመሆኑ ህልውናውን በመንግስት ብቻ ማረጋገጥ እንደማይቻል ተናግሯል፡፡

“ሀብቱ የጋራ በመሆኑ ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል በጥር ወር በሚካሄደውን ዘመቻ እንዲሳተፍ የአርባ ምንጭ ከተማ ወጣቶችን በማስተባበር ላይ መሆናቸውን ገልጿል፡፡

የአባያ ሐይቅ 1 ሺህ 160 ስኩዌር ኪሎ ሜትር ስፋት ያለው ሲሆን በኢትዮጵያ ከጣና ሐይቅ ቀጥሎ በስፋቱ በሁለተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል፡፡