በግድቡ ግንባታ መጓተት ላይ የተጀመረው ተጠያቂነትን የማረጋገጥ ሥራ ተጠናክሮ መቀጠል ይኖርበታል-የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት

600

አዲስ አበባ ታህሳስ 25/2011 በታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ መጓተት ላይ የተጀመረው ተጠያቂነትን የማረጋገጥ ሥራ ተጠናክሮ መቀጠል እንደሚገባ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ገለጸ።

የውሃ ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር በበኩሉ ግድቡ በ2015 ዓ.ም ተጠናቆ ሙሉ ለሙሉ ወደ ሥራ እንደሚገባ ለምክር ቤቱ አስታውቋል።

ምክር ቤቱ የውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር የታላቁን ህዳሴ ግድብ አጠቃላይ ሁኔታና የሥራ አፈፃፃም በተመለከተ ያቀረበውን ሪፖርት በዛሬው እለት አድምጧል።

የምክር ቤቱ አፈ ጉባዔ አቶ ታገሰ ጫፎ በዚህ ጊዜ እንደገለጹት ሚኒስቴሩ በግድቡ ግንባታ ላይ የተስተዋሉ ችግሮችን በዝርዝር የመለየት ሥራ ሰርቶና የጥራት ደረጃውን ጠብቆ እንዲጠናቀቅ የወሰደው የመፍትሄ አቅጣጫ በጥንካሬ የሚነሳ ነው።

በቀጣይም የግድቡ ግንባታ በተያዘለት የጊዜ ሰሌዳ እንዲጠናቀቅ የሚመለከታቸው አካላት በቅርበት ክትትል የማድረጉን ሥራ በትኩረት መስራት እንደሚገባቸው ጠቁመዋል።

በተጓዳኝም በግድቡ ግንባታ ላይ ለጠፉት ጥፋቶች ተጠያቂነትን የማረጋገጥ ሥራ ለሌሎችም አገራዊ ትላልቅ ፕሮጀክቶች ትምህርት በሚሰጥ መልኩ ተጠናክሮ መቀጠል ይኖርበታል ብለዋል።

ህብረተሰቡ ለግድቡ የሚያደርገውን ተሳትፎ እንዲቀጥልና በግድቡ ግንባታ ላይ አመኔታው እንዲጨምር የሚያደርጉ ሥራዎችን መስራት ያስፈልጋል ሲሉም አክለዋል።

ከተፋሰሱ አገራት ጋር የሚደረገው የዲፕሎማሲ ግንኙነት ስራም ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ጠቁመው በግድቡ ዙሪያ የሚደረገው ድርድርና ውይይት የጋራ ተጠቃሚነትን መሰረት ባደረገ መልኩ እንደሚከናወን ጠቁመዋል።

የውሃ፣መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትር ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ በበኩላቸው የግድቡን ግንባታ አጠናቆ ወደ ሥራ ለማስገባት ችግሮችን ለይቶና የጥራት ስራዎች ላይ ትኩረት በማድረግ እየተሰራ ነው ብለዋል።

የልምድ ማነስ፣ ለመማር ዝግጁነት ያለመኖር፣ የፕሮጀክት አስተዳደር ውስንነት፣ የፕሮጀክቱን ጥልቀትና ውስብስብነት በትክክል ተረድቶ አፋጣኝ መፍትሄ ያለመውሰድ ለግድቡ ግንበታ ስራ መጓተት ተጠቃሽ ምክንያቶች መሆናቸውንም ገልጸዋል።

በአሁኑ ወቅት ግንባታውን በተያዘለት የጊዜ ሰሌዳ ለማጠናቀቅም የግድቡ የውሃ ማስተንፈሻ፣ የወንዙን አቅጣጫ ማስቀየሪያ፣ ለተርባይኖች የውሃ ማስተላለፊያ አሸንዳዎችንና መቆጣጠሪያ በሮች ግንባታ የማጠናቀቅ ስራ እየተሰራ ነው።

በተለይም የተበጣጠሱና ለማስተዳደር አስቸጋሪ የሆኑ የኮንትራት ውሎችን የማሻሻል ተግባራት እየተሰሩ መሆናቸውን ጠቅሰዋል።

ይህም የታላቁን ህዳሴ ግድብ በ2013 ዓ.ም 750 ሜጋ ዋት ኃይል የማመንጨትና በ2015 ዓ.ም ግድቡን አጠናቆ ሙሉ ለሙሉ ወደ ሥራ ለማስገባት ያስችላል ሲሉም ገልጸዋል።

በአሁኑ ጊዜ የሲቪል ስራው 82 በመቶ ፣ የኤሌክትሮ ሜካኒካል ስራው 23 በመቶ የደረሰ ሲሆን የግድቡ የግንባታ ፕሮጀክት በአጠቃላይ 65 በመቶ ደርሷል።

እስካሁን ለግድቡ ግንባታ ከቦንድ፣ ከልገሳ፣ ከዳያስፖራ መዋጮና ከልዩ ልዩ ገቢዎች ከ12 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ መገኘቱን ተናግረው፤ በቀጣይም ህዝቡ የሚያደርገውን አስተዋጾኦ አጠናክሮ እንዲቀጥል የሚያደርጉ የተለያዩ ስራዎችን ለመስራት በዕቅድ መያዙን አብራርተዋል።

የሳሊኒ ኮንስትራክሽን እስካሁን ለፈጸመው 82 በመቶ የስራ አፈጻጸም 81 በመቶ ክፍያ የተከፈለ ሲሆን፣ ለብረታ ብረትና ኢንጂነርግ ለፈጸመው 23 በመቶ 65 በመቶ ክፍያ፤ ለ57 በመቶ የምንጣሮ ስራ አፈጻጸም 50 በመቶ ክፍያ እንዲሁም  ለ73 በመቶ የመልሶ ማቋቋም የስራ አደፈፃፃም 64 በመቶ ክፍያ ተፈጽሟልም ተብለዋል።

በሜቴክ ተገዝተው ተበታትነው የነበሩ ንብረቶችን የመሰብሰብና ያጠፉ አመራሮች እንዲጠየቁ የማድረግ ተግባራትም እየተከናወኑ እንደሆነም አክለዋል።