በሀዋሳ ማረሚያ ቤቶች ግጭት እንዲቀሰቀስ አድርገዋል የተባሉ ተጠርጣሪዎች ክስ ተመሰረተባቸው

64

አዲስ አበባ  ታህሳስ 24/2011 በሀዋሳ ማረሚያ ቤቶች የብሄር ግጭት እንዲቀሰቀስ አድርገዋል የተባሉ 67 ተጠርጣሪዎች ላይ ክስ መመስረቱን የፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ አስታወቀ።

ከተጠርጣሪዎች መካከል የከተማዋ የቀድሞ ከንቲባ፣አንድ ከፍተኛ የማረሚያ ቤት አመራርና አምስት የፖሊስ አባላት የሚገኙበት መሆኑም ታውቋል።

የፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ በአገሪቷ አንዳንድ አካባቢዎች ከተከሰቱ ግጭቶች ጋር በተያያዘ ምርመራቸው የተጠናቀቁና በሂደት ላይ ያሉ መዝገቦችን አስመልክቶ ዛሬ መግለጫ ሰጥቷል።

በፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ የድንበር ተሻጋሪና የተደራጁ አገራዊ ጉዳት የሚያስከትሉ ወንጀሎች ዳይሬክተር አቶ ፍቃዱ ፀጋ እንደተናገሩት በሀዋሳ፣ በቤንሻንጉል፣ አሶሳና ቡራዩ ከተሞች በተከሰቱ ግጭቶች የፀጥታ አካላት፣የፖለቲካ ሹመኞችና የቢሮ ሀላፊዎች የተሳተፉበት የወንጀል ድርጊቶች ተፈጽመዋል።

በአሶሳ ከተማ ሰኔ 18 በተከሰተው ግጭት ተሳትፈው የነበሩ የዞኑ የቢሮ ሀላፊዎች በወንጀል ተጠያቂ መሆናቸው መረጋገጡና ያለመከሰሰስ መብታቸው የማስነሳት ሂደት ላይ መሆኑንም አንስተዋል።

በአገሪቱ በተለያዩ አካባቢዎች ብሄርን መሰረት አድርገው ግጭት እንዲከሰት ሲያነሳሱ በነበሩ ተጠርጣሪዎች ላይ የተከፈቱ  መዝገቦች ላይ  የምርመራና የማጣራት ስራ መሰራቱንም ገልጸዋል ።

ከእነዚህም መካከል በሀዋሳ ማረሚያ ቤቶች በወላይታና በሲዳማ ብሄር ተወላጅ ታራሚዎች መካከል ግጭት እንዲከሰት ካነሳሱ ተጠርጣሪዎች ጋር በተያያዘ በሶስት መዝገቦች ላይ  ምርመራ ሲደረግ ቆይቶ በሁለቱ ላይ ክስ ተመስርቷል ብለዋል።

አቶ ፍቃዱ እንደገለጹት የማረሚያ ቤቱ አመራሮች፣ የፖሊስ አባላትና ታራሚዎች የተሳተፉበት ወንጀል ጋር በተያያዘ 67 ተጠርጣሪዎች ላይ ክስ ተመስርቷል።

ቀደም ሲል በግጭቱ ወቅት የሀዋሳ ከተማ  ከንቲባ የነበሩት ግለሰብ አንዱን ብሄር ከሌላው ጋር እንዲጋጭ በማነሳሳት ወንጀል ተጠርጥረው በማስረጃ በመረጋገጡ እሳቸውን ጨምሮ 32 ተጠርጣሪዎች ላይ ክስ  መመሰረቱንም አቶ ፍቃዱ ተናግረዋል።

እንደ አቶ ፍቃዱ ገለፃ በዚሁ ወንጀል ተጠርጥረው በቁጥጥር ስር ያልዋሉ ግለሰቦችም በሌሉበት ክሳቸው እንዲታይ በማለት ለጥር 15 ቀን 2011 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ተይዟል።

በሀዋሳ ከተማ በተከሰተው ግጭት ጋር በተያያዘ 75 ተጠርጣሪዎችን የያዘ መዝገብ በምርመራ ሂደት ላይ መሆኑንም አክለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም