“ ሀኪም ቤቱ ይታከም ! ”

1319

መለሰ ይነሱ ባህርዳር (ኢዜአ)

ጠቅላላ  ሀኪም  ዶክተር ሰርካለም ዘውዴ በባህር ዳር ፈለገ ህይወት ሪፈራል ሆስፒታል  የካንሰር ህክምና ማዕከል መደበኛ ስራቸውን በማከናወን ላይ ናቸው።

አንድ ቀን ጧት ወደ ሆስፒታሉ ጎራ ስል ዶክተር ሰርካለምና ባልደረቦቻቸው ባልተለመደ መልኩ  በግቢው ተሰባስበው ቆመው አየኋቸው። የስራ ማቆም አድማ መሆኑ ነው ።

እኔም አዲስ ክስተት ያገጠመኝ በመሆኑ ወደ ዶክተር ሰርካለም ጠጋ ብየ ምን ሆናችሁ ነው ተሰልፋችሁ የቆማችሁት  ስራ አትገቡም እንዴ?… የሚሉና ሌሎች ተያያዝ ጥያቄዎችን አቀረብኩላቸው።

የስራ ማቆም አድማ አድርገን ነው በማለት ንግግራቸውን በስሜት ጀመሩ ። “የስራ ማቆም አድማ ለማድረግ የተገደድነው ሰሚ ስላጣንና የችግሩን አስከፊነት ለማሳየት ነው ” ሲሉም አከሉበት ።

 የስራ ማቆም አድማው ምክንያት ሆስፒታሉ ከተቋቋመ ከ50 ዓመታት በላይ ያስቆጠረ ቢሆንም  የካንሳር፣ ቲቢና ሌሎች የአገልግሎት መስጫ ጊዜያቸው ያለፈባቸው መድሃኒቶችና ደረቅ ቆሻሻዎች የሚወገዱት ሳይንሳዊ ባልሆነ መልኩ በመሆኑ ጤናችንን አደጋ ላይ በመውደቁ ነው ይላሉ።

 አሳሳቢ የሚያደርገው የማስወገጃ ቦታው በሆስፒታሉ መሀል ላይ በመሆኑና በየቀኑ በሚቃጣለው ቆሻሻ ምክንያትም ጪስና ሽታው ባለሙያዎችንና ተገልጋዩን ህብረተሰብ በመረበሽ  ላልተፈለገ የጤና እክል እየዳረገን ተቸግረናል ባይ ናቸው ።

“እኛ አክመን እናድናለን ስንል ለሌላ በሽታ መዳረጋችን መቆም አለበት ። የሚቃጠሉ መድሃኒቶችም ለሌላ በሽታ  መንስኤ መሆን የለባቸውም  ” ሲሉ ነው የገለጹት ። የቆሻሻው ጭስ ሽታ ለካንሰር፣ቲቢ፣ አስምና ሌሎች ተያያዥ በሽታዎች መንስኤ ሊሆኑ እንደሚችሉም ነው የተናገሩት  ።

ሆስፒታሉ ሳይንሳዊ የሆነ የቆሻሻ ማስወገጃ ስርአት እንዲጠቀምና ተገቢ  ቦታ እንዲያመቻች ሃኪሞች በተደጋጋሚ ቢጠይቁም  ከአቅሜ በላይ ነው በሚል ሰበብ  ምላሽ መስጠት  ባለመቻሉ ችግሩ ተባብሶ ቀጥሏል ብለዋል።

እኔም የጉዳዩን እውነተኛነት ለማረጋገጥ የቆሻሻ አወጋገድ ስርዓቱን በተደጋጋሚ እንደተመለከትኩት ከቀኑ ዘጠኝ ሰዓት በኋላ ዘወትር እንደሚቃጠልና ከመጥፎ ሽታ ባሻገር ጭሱ በመስኮቶች እየገባ ሀኪሞቹ እንደሚረበሹ መመልከት ችያለሁ። መስኮቶቹን በወረቀትና በተለያዩ ጨርቆች ለመከላከል ሙከራ በማድረግ አገልግሎት ሲሰጡ ታዝቤያለሁ።

 “ተፎካካሪ እረኞች አንተ መልሳቸው፣ አንተ መልሳቸው እልህ ሲያያዙ ከብቶች እርቀዋል ዋጋ ሊያስከፍሉ “ እንዲሉ ነገሩ ተባብሶ እስከ ስራ ማቆም አድማ ለመድረስ ያስቻለው ችግሩን ለመፍታት  ሃላፊነቱን የሚወስድ አካል ባለመገኘቱ ነው።

 በጉዳዩ ዙሪያ ሀኪሞች ለምን ሰሚ አጡ ? የሚል ጥያቄ ለማንሳት ወደ ሆስፒታሉ አመራሁ ። የቀድሞው ሜዲካል ዳይሬክተር ከሃላፊነታቸው ተነስተው በአዲስ ተተክተዋል ። ሁለቱንም ሳነጋግር ግን መልሶቻቸው ” ዱባና ቅል አበቃቀላቸው ለየቅል ” ሆነብኝ ።

በቅርቡ ከሃላፊነታቸው የተነሱት ዶክተር መልካሙ ባየ የሚሉት ሆስፒታሉ ችግሩን ሳይፈታው የቆየው ከአቅሙ በላይ በመሆኑ ነው ይላሉ ። ምክንያቱን ሲያብራሩ ደግሞ ለቆሻሻ ማስወገጃ ቦታ  የማመቻቸትና ምቹ ሁኔታዎችን መፍጠር የከተማ አስተዳደር ሃላፊነት ነው ።

 “ የከተማ አስተዳደሩ የቆሻሻ ማስወገጃ ቦታ እንዲሰጠን ብንጠይቅም ቦታ ለማግኘት በራሳችሁ ካሳ ከፍላችሁ ካልሆነ በስተቀር አታገኙም ” የሚል ምላሽ መስጠቱን አስረድተዋል።

በቅርቡ የሜዲካል ዳይሬክተርነት ቦታውን የተረከቡት ዶክተር  ሸጋው ማሩ ግን የተለየ ሃሳብ አላቸው ። የራሱን ቆሻሻ ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ ማስወገድ ያለበት እራሱ ሆስፒታሉ እንጂ ሌላ አካል አይደለም ባይ ናቸው ።

እንዲያውም ሆስፒታሉ ሌሎች ተቋማት ጭምር ቆሻሻን በዘመናዊ መንገድ የሚያስወግዱበት ስልት ማስተማር ሲገባው የራሱን ቆሻሻ ለዓመታት ይዞ መቆየቱ ከተጠያቂነት አያድነውም ብለዋል ።

ችግርን ወደ ሌላ በመወርወር መፍትሔ አይገኝም የሚሉት ዶክተር ሸጋው በሆስፒታሉ ቸልተኝነት ቀላል የማይባል ጉዳት እያደረሰ መምጣቱ ተገቢ አልነበረም ።

አሁን ግን ሆስፒታሉ ዘመናዊ የቆሻሻ ማቃጠያ ቴክኖሎጂ (ኢንሲሌተር) ለመገንባት የጥናት ስራው ተጠናቋል ። በጥናቱ መሰረት 5 ሚሊዮን ብር ወጪ የሚጠይቅ ቴክኖሎጂ እንደሚያስፈልግ የተረጋገጠ ሲሆን የቦታ መረጣ ዝግጅትም ተደርጓል ።

 የከተማው  አስተዳደር አካባቢ ጥበቃ ጽዳትና ውበት ጽህፈት ቤት  በበኩሉ  “የጤና ተቋማት የቆሻሻ አወጋገድ የራሱ የሆነ ሳይንሳዊ መመሪያ ስላለው ከከተማ አስተዳደሩ ጋራ የሚያገናኝ ምንም አይነት ምክንያት የለውም ” የሚል ምላሽ ሰጥቷል ።

የጽህፈት ቤቱ ሃላፊ አቶ ዳዊት የኔው እንደገለጹት  የከተማ አስተዳደሩ አደገኛ ያልሆኑና አካባቢን ሊያቆሽሹ ይችላሉ የተባሉ ከተለያዩ የንግድና መሰል ተቋማት የሚወጡ ቆሻሻዎቸን የማስወገድ ሃላፊነት ብቻ ነው ያለበት።

አደገኛ የሚባሉና በሰውና በእንስሳት ላይ የከፋ የጤና ችግር ሊያደርሱ የሚችሉ  ከጤና ተቋማት የሚወጡ ቆሻሻዎች የሚወገዱት በራሳቸው በጤና ተቋማት ነው ። ለቆሻሻ ማሰወገጃ የሚሆን ቦታ ለማግኘትም ካሳ የመክፈል ግዴታ የጤና ተቋማቱ ነው ሲሉ አብራርተዋል ።

ሆስፒታሉ በራሱ የአስተዳደር ድክመት  ምክንያት እራሱ መፍታት የሚችለውን ችግር  በሌላ አካል ማመካኘት የለበትም አሁንም አፋጣኝ መፍትሄ መውሰድ ያለበት ራሱ ሆስፒታሉ ነው ።

አለም አቀፍ የጤና ተቋማት የቆሻሻ አወጋገድ ስርዓትም የጤና ተቋማት ቆሻሻቸውን በራሳቸው ሳይንሳዊ መንገድ ተጠቅመው ማስወገድ እንዳለባቸው ነው የሚያስረዳው ።

የፈለገ ህይወት ሪፈራል ሆስፒታል ለመሬት ካሳ ክፍያ የለኝም ማለት አይጠበቅበትም። እንደማንኛውም የመንግስት ተቋም በጀት ስለሚመደብለት አብቃቅቶና ከእርዳታ ድርጅቶች ገንዘብ  አፈላልጎ መፍትሄ ማምጣት ግዴታው ነው በማለት ።

የፈለገ-ህይወት ሪፈራል ሆስፒታል በአማራ ክልል ከሚገኙ ሆስፒታሎች መካከል እድሜ ጠገቡ ቢሆንም እስከ አሁን ድረስ ሳይንሳዊ የቆሻሻ አወጋገድ ስርአት አለመከተሉ ለትዝብት የሚዳርግ ነው።

ከህመማቸው ለመፈወስ ወደ ሆስፒታሉ የሚመጡ ህሙማን ሳያውቁት ሌላ ተጨማሪ በሽታ ይዘው እንዳይሄዱ የሚመለከተው አካል ችግሩን በፍጥነት መፍታት ይጠበቅበታል ። ለዚህ ደግሞ መገፋፋት ሳይሆን ተቀራርቦና ተነጋግሮ ለጋራ ችግር የጋራ መፍትሄ ማፈላለግ እንደሚገባ የብዙዎች እምነት ነው – መልካም ንባብ  ።