የአምቦ አውቶብስ መነኸሪያ ግንባታ መዘግየት ቅሬታ ፈጥሯል

62

አምቦ ታህሳስ 24/2011 የአምቦ አውቶብስ መነኸሪያ ግንባታ  ባለፈው ዓመት ተጠናቆ ለአገልግሎት ይበቃል ቢባልም እስካሁን ስራ አለመጀመሩ ቅሬታ እንዳሳደረባቸው አሸከርካሪዎችና ነዋሪዎች ተናገሩ፡፡

የመነኸሪያው  ግንባታ የተጀመረው  በ2007 ዓ.ም. እንደሆነ ተመልክቷል፡፡

በአምቦ  የህዝብ ማመላለሻ ሚኒባስ አሽከርካሪ  ወጣት አብርሃም ደበላ እንዳተናገረው  አሁን ያለው የአውቶብስ መነኸሪያና የተሽከርካሪው ቁጥር አልተመጣጠነም፡፡ 

በመገንባት ላይ ያለው አዲሱ የአውቶብስ መነኸሪያ ባለፈው ዓመት ለአገልግሎት ይበቃል ተብሎ የነበረ ቢሆንም እስከ አሁን ድረስ ባለመጠናቀቁ መቸገራቸውን ተናግሯል፡፡

ችግሩ በተለይ ጥዋት-ጥዋት ግማሽ የሚሆኑ ተሸከርካሪዎች ከትራንስፖርት ባለስልጣኑ ህግና ስርዓት ውጪ መንገድ ዳር ሆነው ተሳፋሪዎችን ለመጫን እየተገደዱ በመሆኑ አፋጣኝ መፍትሄ እንዲሰጠው ጠይቀዋል።

ሌላው አሽከርካሪ ወጣት ኤፍሬም አበበ በበኩሉ "የመነኸሪያው ስፋት ከተሽከርካሪው ብዛት ጋር የማይመጣጠን  በመሆኑ በተፈጠረው  ጥበት ምክኒያት ተሽከርካሪ ለመዞርና መነኸሪያ ውስጥ ገብቶ ለመውጣት ከሌላ ተሽከርካሪ ጋር እየተጋጨ ለወጪ እየተዳረግን ነው " ብሏል፡፡

የአዲሱ መነኸሪያም ግንባታም  ረጅም ጊዜ መውሰዱን ጠቁሟል፡፡

የሚመለከተው አካል የተጓተተውን  ግንባታ በአፋጣኝ በመጨረስ የአሽከርካሪዎችንና የህብረተሰቡን ችግር መፍታት እንደሚገባውም አመልክቷል፡፡

መንግስት የህብረተሰቡን የረጅም ጊዜ የመልካም አስተዳዳር ጥያቄ ለመፍታት ከአምስት ዓመት በፊት የመነኸሪያውን ግንባታ ሲጀምር ተደስተው እንደነበር የተናገሩት ደግሞ የከተማዋ ነዋሪ  አቶ ተስፋዬ ቦንሣ ናቸው፡፡

ሆኖም ግንባታው በታሰበለት ጊዜ ባለመጠናቀቁ  ቅሬታ እንዳሳደረባቸውና በመንግስት በኩል ትኩረት ተሰጥቶት አፋጣኝ  መፍትሄ ማመቻቸት እንደሚገባ አመልክተዋል፡፡

የከተማው  ነዋሪ  ወይዘሮ ጫልቱ በበኩላቸው " ወደ መነኸሪያ ሄጄ ትራንስፖርት ለመያዝ ሳስብ ገና ለገና እሳቀቃለሁ ምክንያቱም እዚያ ያለው ግፊያና መጨናነቅ ያሳስበኛል " ብለዋል፡፡

አዲሱ መነኸሪያ አገልግሎት ቢጀምር እየበዛ የመጣውን ተሸከርካሪና ተገልጋይ  በተገቢው መንገድ በማስተናገድ አሁን ያለው መጨናነቅና እንግልት ሊያስቀር እንደሚችል አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡   

ስለጉዳዩ የተጠየቁት የአምቦ ከተማ ትራንስፖርት ባለስልጣን ኃላፊ አቶ ቦጃ ወልደ ሚካኤል በሰጡት ምላሽ  ቅሬታው ተገቢ መሆኑንና ችግሩን ለመፍታት የተጀመረው  አዲሱ  የአውቶብስ መነኸሪያ ግንባታ በተቋራጩ ምክንያት ስራው መጓተቱን ገልጸዋል።

ኃላፊው እንዳሉት ተቋራጩ በ2007 ዓ.ም ግንባታውን በጀመረበት ወቅት በሶስት ዓመታት ውስጥ ለማጠናቀቅ በገባው ውል መሰረት ማጠናቀቅ አልቻለም፡፡

" ከኮንትራክተሩ ጋር ዳግም በተደረገ ስምምነት በዚህ ወር ግንባታውን አጠናቆ እንደሚያስረክበን ብንዋዋልም ባደረግነው የመስክ ምልከታ ግን በዚህ ወቅት የሚጠናቀቅ አለመሆኑን ተመልክተናል" ብለዋል፡፡

ተቋራጩ  ስራውን በአግባቡ እያከናወነ ባለመሆኑ  እርምጃ በመውሰድ ለህብረተሰቡ አፋጣኝ ምላሽ የሚሰጥ መሆኑን ኃላፊው አስረድተዋል፡፡  

አላስ ኮንስትራክሽን የተባለው የተቋራጩ ድርጅት ስራ አስኪያጅ ኢንጅነር ቴዎድሮስ ነጋሽ ተጠይቀው በሰጡት ምላሽም ግንባታው መጓተቱን አምነው  ለዚህም  ኪሣራውን ጭምር በመሸፈን በተሰጣቸው የመጨረሻ ማስጠንቀቂያ መሠረት በሶስት ወራት  ውስጥ ለማጠናቀቅ እየሰሩ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

85 በመቶ ላይ የሚገኘውን የአውቶብስ መነኸሪያው ግንባታ ቀሪው የአስፋልት ማንጠፍ ስራንም ለማካሄድ አስፈላጊውን መሣሪያ ማስገባታቸውን ተናግረዋል፡፡

ከመነኸሪያው  ውጪ ያለውን የድንጋይ ማንጠፍ ስራና የአጥር ስራ ለማከናወንም የመብራት ምሶሶዎች  በአፋጣኝ ከተነሰላቸው ስራውን በውሉ መሰረት ማጠናቀቅ እንደሚችሉ ኢንጅነሩ አስታውቀዋል፡፡

የትራንስፖርት ባለስልጣን መስሪያ ቤት በበኩሉ ምሶሶዎቹ በአፋጣኝ እንዲነሱ ለከተማው ኤሌክትሪክ ኃይል ዲስትሪክት ደብዳቤ ማስገባቱና ክትትል በማድረግ እንደሚያስፈጽም ገልጿል፡፡  

ነባሩ የአምቦ  አውቶብስ መናኸሪያ በመጥበቡ ምክንያት ይህንን ችግር ሊፈታ የሚችል ሌላ አዲስ ግንባታ በ56 ሚሊዮን ብር በጀት እየተካሄደ መሆኑንና ባለፈው ዓመት ተጠናቆ ለአገልግሎት እንደሚበቃ ኢዜአ በወቅቱ ዘግቦ ነበር፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም