ጠቅላይ ሚኒስትሩ በጎረቤት አገሮች የሚያደርጉት ጉብኝት አጋርነትን ያሳድጋል

64
አዲስ አበባ ሚያዝያ 25/2010 ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ በጎረቤት አገሮች የሚያደርጉት የስራ ጉብኝት ከአገሮቹ ጋር ያለውን ታሪካዊና ስትራቴጂካዊ አጋርነት ለማስቀጠል ሚናው የጎላ መሆኑን የመንግሥት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ገለጸ። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በአገሪቱ በተለያዩ አካባቢዎች ከኅብረተሰቡ ጋር ያደረጉት ውይይት ለብሔራዊ መግባባት አቅም መፍጠሩንም አስታውቋል። ዶክተር አብይ አህመድ በጠቅላይ ሚኒስትርነት ከተሰየሙ ትላንት አንድ ወር የሞላቸው ሲሆን በአሁኑ ወቅት በሱዳን የሁለት ቀናት ይፋዊ የሥራ ጉብኝት በማድረግ ላይ ናቸው። በአንድ ወር ጊዜ ውስጥም ከአገር ቤት ጀምሮ እስከ ጎረቤት አገሮች ድረስ አበረታች ሥራ መሥራታቸውን ነው የጽህፈት ቤቱ ኃላፊ ሚኒስትር አቶ አህመድ ሺዴ የተናገሩት። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በጂቡቲ ይፋዊ የሥራ ጉብኝት የጀመሩት ከአገሪቱ ጋር ባለው የጥቅም ትስስርና ስትራቴጂካዊ ቁርኝት አንጻር መሆኑን አስምረውበታል። በዚህም ከጂቡቱ ጋር የልማት ሥራዎችን በስፋት በመሥራት ምጣኔ ኃብታዊ ውህደቱን ለማቀላጠፍ ስምምነት ተደርሷል፤ 'ይህም ትልቅ ዲፕሎማሲያዊ ድል ነው' ብለዋል። በተመሳሳይ ኢትዮጵያና ሱዳን በተለያዩ መስኮች ላይ በትብብር እየሰሩ መሆኑንና በታላቁ ህዳሴ ግድብ ሁለቱ አገሮች ተመሳሳይ አቋም ያላቸው መሆኑን ገልጸዋል። በቀጠናው ሰላምና ደኅንነት ጉዳይ አጋርነቱ ጠንካራ መሆኑን ያነሱት አቶ አህመድ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጉብኝት ይህንን ሁለንተናዊ አብሮነት በማሳደግ ረገድ አስተዋጽዖ እንዳለው ጠቁመዋል። "መሪዎቹ በሚያደርጓቸው ውይይቶች ይኸው ጠንካራ ግንኙነት ወደ ላቀ ደረጃ ይለወጣል የሚል እምነት አለን፤ በተለይም በመሰረተ ልማት በንግድ፣ በትራንስፖርት፤ በሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት የሁለቱን አገሮች ግንኙነት የሚያጠናክሩ ዲፕሎማሲያዊ ውይይቶች ይካሄዳሉ ተብሎ ይገመታል'' ብለዋል። ከዚህ ባለፈ በአገር ቤት በክልሎች ተዘዋውረው ከተለያዩ የማኅበረሰብ ተወካዮች ጋር ቀጥተኛ የተሳትፎ መድረኮችን በማዘጋጀት ሰፋ ያለ ውይይት ማድረጋቸውን ተናግረዋል። ህብረተሰቡም ከልማት፣ ከመልካም አስተዳደርና ከሰላም ጋር የተያያዙ ጥያቄዎችን ግልጽና ዴሞክራሲያዊ በሆነ መልኩ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ማቅረቡን ጠቁመዋል። ለጥያቄዎቹም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተገቢውን ምላሽና ማብራሪያ መስጠታቸውን ጠቅሰው ይህም አገራዊ መግባባት በመፍጠር ረገድ ሚናው የጎላ መሆኑን ገልጸዋል። አገራዊ መግባባቱም በተለይም ሁለተኛውን የእድገትና የትራንስፎርሜሽን እቅድን በአግባቡ ለመተግበር እገዛ ያደርጋል ነው ያሉት። ከዛም ባለፈ ለአገራዊ አንድነት ያለው ፋይዳ ከፍተኛ መሆኑን በመግለጽ። የጽህፈት ቤቱ ኃላፊ ሚኒስትር አቶ አህመድ "አጠቃላይ በሕዝቦች መካከል ያለውን ትስስርና ወንድማማችነት በሁሉም አካባቢ ሰላማችን እንዲረጋገጥ ከማድረግ አንጻር ጥሩ መግባባት የተፈጠረበት ነው ማለት ይቻላል፤ ለቀጣይ የጂቡቲ እቅዳችን መሳካት ከፍተኛ አገራዊ መግባባት የተፈጠረበት እንዲሁም በአገር ግንባታ ጉዟችን ወይም አገራዊ መግባባት በመፈጠር ረገድ ውጤታማ ነበር " በማለት ገልጸዋል። ጎን ለጎንም ሰላምን ለማስፈን በህዝቦች መካከል ያለውን ትስሰር ይበልጥ ለማጎልበት ሁነኛ ሚና መጫወቱን አስረድተዋል። በተለያዩ አከባቢዎች የሚከሰቱ ግጭቶችና አለመግባባቶች በአብሮነትና በወንድማማችነት ስሜት ለመፍታት አቅጣጫ ያስቀመጡበት ውይይት መሆኑንም ገልጸዋል። የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይና የደህንነት ፖሊሲ ለጎረቤት አገሮች ቅድሚያ በመስጠቱ አገሪቱ ባለፉት ዓመታት ከጎረቤቶቿ ጋር ጠንካራ ግንኙነት መፍጠር ችላለች።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም