በቡራዩና አዲስ አበባ አንዳንድ ቦታዎች ላይ በተፈጠረው ግጭት በተጠረጠሩት 109 ግለሰቦች ላይ ክስ ተመስርቷል

69

አዲስ አበባ ታህሳስ 24/2011 በቡራዩና አዲስ አበባ አንዳንድ ቦታዎች ላይ በተፈጠረው ግጭት በተጠረጠሩት 109 ግለሰቦች ላይ ክስ መመስረቱን የፌዴራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ   አስታወቀ።

የፌዴራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ በግጭቱ ላይ በተጠናቀቀው ምርመራ ውጤት እና የገና በዓል አስመልክቶ ይቅርታ በተደረገላቸው የህግ ታራሚዎችን በሚመለከት ዛሬ መግለጫ ሰጥቷል።

የፌዴራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ዝናቡ ቱኑ በመግለጫቸው እንዳሉት በቡራዩና አዲስ አበባ መስከረም 2011ዓ.ም መጀመሪያ ላይ የኦነግ አመራሮች አቀባበል ጋር ተያይዞ  በተፈጠረው ግጭት ባጠቃላይ 649 ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር ውለው ነበር።

ከተጠርጣሪዎቹ ውስጥም 321 ግለሰቦች በወንጀሉ አለመሳተፋቸው ተጣርቶ ተለቀዋል ብለዋል።

ከነዚሁ ተጠርጣሪዎች 126 ደግሞ ግርግሩን ተጠቅመው በዝርፊያ፣ ስርቆት እና ሌሎች ደንብ በመተላለፍ ላይ የተሳተፉ መሆኑን ገልጸው፤ እነዚህ ተጠርጣሪዎች በክልሉ እንዲዳኙ ተላልፈው መሰጠታቸውንና 13ቱ ደግሞ ምንም ክስ ሳይመሰረትባቸው መለቀቃቸውን ተናግረዋል።

ክስ ከተመሰረተባቸው 109 ግለሰቦች መካከልም 81 የተያዙ ሲሆን፥ 28 በሌሉበት ክስ ተመስርቶባቸውና የፍርድ ቤት ማዘዣ ወጥቶባቸው እየታደኑ ነው ብለዋል።

እንደ አቶ ዝናቡ ገለጻ ወንጀሉ ሲጣራም የወንጀሉ መነሻ በአዲስ አበባ ወጣቶችና ለኦነግ አቀባበል ዝግጅት እያደረጉ ባሉ ቄሮዎች መካከል "ቄሮዎች አዲስ አበባ አትገቡም" በሚል መነሻ መሆኑን ተናግረዋል።

ለሁከቱ መነሻ የሆነውም በሀሰተኛ ወሬዎች ሰዎችን ለሁከት ማነሳሳት መሆኑን አስምረውበታል።

በዚህም ተጠርጣሪዎቹ በግድያና የግድያ ሙከራ ወንጀሎችና በውንብድና ወንጀሎች መከሰሳቸውንም ገልጸዋል።

በተከሰተው ግጭትም በቡራዩ 37 ሰዎች፣ በአዲስ አበባ ደግሞ 28 ሰዎች ለህልፈት ተዳርገዋልም ብለዋል።

ክስ ከተመሰረተባቸው መካከልም በቡራዩ 4 የፖሊስ አባላት፣ እንዲሁም በአዲስ አበባ 1 የፖሊስ ጣቢያ ኃላፊ የሆነች ሴት ፖሊስ እንዳሉበትም ተናግረዋል።

ኃላፊው በመግለጫቸው አክለውም የዘንድሮን የገና በዓል ምክንያት በማድረግ ለ538 የፌዴራል የህግ ታራሚዎች ይቅርታ መደረጉን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም