ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ለመንግስት ገቢ ያልተደረገ ታክስ ገቢ እንዲያደርግ ተጠየቀ

55

አዲስ አበባ ታህሳስ 24/2011 የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ለዳኞች ሲከፈል ከነበረው አበል ለመንግስት ገቢ ያልተደረገ ከአራት ሚሊዮን ብር በላይ ተመላሽ እንዲያደርግ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አሳሰበ።

በምክር ቤቱ የመንግስት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የጠቅላይ ፍርድ ቤቱን የ2009 ዓ.ም በጀት ዓመት የሂሳብ ኦዲት ሪፖርት የፌዴራል ዋና ኦዲተር በተገኘበት ውይይት አካሂዷል።

በውይይቱም በፌደራል ዋናው ኦዲተር መስሪያ ቤት ከመመሪያ ውጪ የተከፈለ የዳኞች አበልና ጨረታ ሳይወጣ የተፈጸመ የግንባታ ግዥ መፈፀሙ ተረጋግጧል።

የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ አቶ መሐመድ ዩሱፍ እንደገለጹት ዳኞች ከደሞዛቸው ጋር ተደምሮ ለቤት አበል ከሚከፈላቸው መቀነስ የነበረበት ከአራት ሚሊዮን ብር በላይ ታክስ በኦዲት ሪፖርት ተገኝቷል።

ጨረታ ሳይወጣ ያለምንም ውድድር የ10 ሚሊዮን ብር የግንባታ ግዥ ለአንድ ድርጅት በመስጠት ክፍያ መፈፀሙንና የንብረት አያያዝ ላይ ጉድለት መታየቱም ተመልክቷል።

በመሆኑም ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ያለአግባብ ወጪ የተደረጉ ሃብቶችን እንዲመለሱና ከሃብት ብክነት ጋር ግንኙነት ያላቸው አከላት ላይ እርምጃ እንዲወስድ ቋሚ ኮሚቴው አሳስቧል።

በዋናው ኦዲተር በሚሰጠው ግብዓትና አስተያየት መሰረት የጀመራቸውን የእርምት እርምጃዎች አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ተመልክቷል።

የፌዴራል ዋና ኦዲተር አቶ ገመቹ ዱቢሶ በበኩላቸው በጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ለዳኞች ሲከፈል የነበረው የቤት አበልና ያለጨረታ የተፈፀመው የግንባታ ግዥ ከመመሪያ ውጭ መሆኑን  ተናግረዋል።

ይህንን ተከትሎ ተቋሙ በቀጣይ የሚወስዳቸውን የማስተካካያ እርምጃዎች በየሩብ ዓመቱ ማሳወቅ ይኖርበታል ብለዋል።

በቀጣይም የፋይናንስና የወጪ አስተዳደርን ስርዓት ባለው መልኩ ለማካሄድ የወጡትን አዋጆችና መመሪያዎች ተከትሎ መስራት አለበት ሲሉ አሳስበዋል።

የጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ወይዘሮ መዓዛ አሸናፊ በበኩላቸው ከቋሚ ኮሚቴውና ከዋና ኦዲተር መስሪያ ቤት የተሰጣቸውን ምክረ ሃሳብና አስተያየትን እንደ ግብዓት በመጠቀም እንደሚሰሩበት ተናግረዋል።

ፍርድ ቤቱ ህግና ደንብን ተከትሎ በመስራት ለሌሎች ተቋማት አርያ እንዲሆን እንደሚሰሩና የእርምት እርምጃዎችንም እንደሚወስዱ አረጋግጠዋል።

ይሁን እንጂ ከዳኞች የቤት አበል ክፍያ ለመንግስት ገቢ መደረግ የነበረበትን ታክስ ለማስመለስ በወቅቱ የነበሩ ዳኞች ጡረታ መውጣት፣ በህይወት አለመኖር፣ ከስራ መልቀቅና የመሳሰሉት ችግሮች እንቅፋት እንደሚሆኑባቸው አመልክተዋል።

በጠቅላይ ፍርድ ቤቱ የሚፈቱ የኦዲት ግኝቶች ላይ እርምጃ መውሰድ እንደተጀመረ ተናግረው ከፍርድ ቤቱ አቅም በላይ የሆኑትን ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን ለመፍታት እንደሚሰሩም አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም