ኢትዮጵያ የድርድሩ አቅጣጫ ሚዛኑን እንዲጠብቅ አድርጋለች

1500

አዳማ ታህሳስ 24/2011 ኢትዮጵያ 24ኛው ዓለም አቀፍ የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ ባሳለፋቸው ውሳኔዎች ላይ ፍላጎቶቿ እንዲካተቱና የድርድሩ አቅጣጫ ሚዛኑን እንዲጠብቅ ገንቢ ሚና መጫወቷን  የአካባቢ ደንና የአየር ንብረት ለውጥ ኮሚሽን ገለጸ።

በኮሚሽኑ የአየር ንብረት ለውጥና ብዝሃ ህይወት  ዋና ዳይሬክተር አቶ ንጉሱ ለማ እንዳሉት  የተባበሩት መንግስታት የአየር ንብረት ለውጥ አለም አቀፋዊ ስምምነት እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ1992  በአባል አገራት መካከል የተደረሰ ነው ።

አባል አገራቱ ከዚህ ስምምነት በኋላ ድርድሮቻቸውን በመቀጠል እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ1997 ለስምምነቱ ማስፈፀሚያ የኪዮቶ ፕሮቶኮል እንዲሁም   በ2015 የፓሪስ ስምምነት ላይ መድረስ ችለው ነበር ።

አባል አገራቱ የፓሪሱን ስምምነት ወደ ተግባር መለወጥ የሚያስችሉ የስራ መመሪያዎችን አፅድቀው ለማውጣት ላለፉት ሶስት ዓመታት ቢያንስ በዓመት ሁለት ጊዜ እየመከሩና እየተደራደሩ መቆየታቸውን  አቶ ንጉሱ አስረድተዋል።

ዘንድሮ በፖላንድ ፕሬዚዳንትነት በካቶዊች ከተማ  ከሁለት ሳምንት በፊት በተካሄደው  24ኛው የአባል አገራት የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ ላይ አባል አገራት እልህ አስጨራሽ ድርድር ማድረጋቸውንም ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ በጉባኤው በአካባቢ ደንና የአየር ንብረት ለውጥ ኮሚሽን የሚመራ ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት የተወጣጣ  የልኡካን ቡድን አሳትፋለች፡፡

የልኡካን ቡድኑ በአንድ በኩል የኢትዮጵያን ብሄራዊ ጥቅምና ፍላጎት ለማስጠበቅ በሌላ በኩል ደግሞ በዝቅተኛ የእድገት ደረጃ ላይ የሚገኙ 48 አገራትን በመምራት የድርድሩ አቅጣጫ ሚዛኑን እንዲጠብቅ ከፍተኛ ሚና መጫወቷን ዋና ዳይሬክተሩ ተናግረዋል ።

የልኡካን ቡድኑ በተጨማሪም በ11 የሁለትዮሽ መድረኮችና  በ25 የጎንዮሽ ስብሰባዎችን ላይ በመሳተፍ የኢትዮጵያን ልምድና መልካም ተሞክሮ በማቅረብና የሌሎችን ልምድ በመቅሰም  ኃላፊነቱን በብቃት መወጣቱን ገልጸዋል።

በጉባኤው የተላለፉት ውሳኔዎች ኢትዮጵያን  በፋይናንስ ፣ በቴክኖሎጂና በአቅም ግንባታ የሚገባትን ጥቅም እንድታገኝ ያገዛት መሆኑን የተናገሩት ደግሞ በኮሚሽኑ የአየር ንብረት ለውጥ ትግበራ ማስተባበሪያ ዳይሬክተር ጄነራል አቶ ደባሱ ባይለየኝ ናቸው፡፡

“የፓሪሱን ስምምነት ለመተግበር እንዲያግዙ በ24ኛው የአየር ንብረት ጉባኤ የተላለፉ ውሳኔዎች በአንድ በኩል ያደጉ አገራት ለአየር ንብረት ለውጥ የሚሰጡትን ገንዘብ በግልፅ እንዲያሳውቁ በሌላ በኩል ደግሞ ታዳጊ አገራት የተሰጣቸውን ገንዘብ ለምን ስራ እንዳዋሉት የሚጠይቅ የግልፅነትና የተጠያቂነት አሰራር ያካተተ ጭምር ነው “ብለዋል ።

በኮሚሽኑ ዋና የአየር ንብረት ለውጥ ተደራዳሪ ወይዘሪት ሰላማዊት ደስታ በበኩሏ  በድርድሩ በርከት ያለ ካርቦን በሚለቁ አገራት ላይ ጠንከር ያለ ጫና ማሳደር መቻሉን ገልጸዋል።

ተደራዳሪዋ እንዳለችው በአንፃሩ ደግሞ በሚለቀቀው የካርቦን መጠን ለጉዳት የሚዳረጉት ታዳጊ አገሮች ፍላጎታቸውን ታሳቢ ያደረገ ድጋፍ እንዲያገኙ ምቹ ሁኔታ ተፈጥሯል።

“ኢትዮጵያም የሚገባትን ድጋፍ የምታገኝ ሲሆን የካርቦን ልቀቷን በ64 በመቶ ለመቀነስ ጠንክራ መስራት አለባት ” ብላለች።

24ኛው የአባል አገራት የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ ያስገኘው ውጤትና ለኢትዮጵያ የሚኖረው እንድምታ በተመለከተ ዛሬ በአዳማ ከተማ ለባለድርሻ አካላት ገለፃ ተደርጓል።