በማእከላዊ ጎንደር በግጭት ምክንያት የተዘጉ ትምህርት ቤቶች እንዲከፈቱ እየተሰራ ነው

1244

ጎንደር ታህሳስ 24/2011 በማእከላዊ ጎንደር ግጭት ተከስቶባቸው በነበሩ አካባቢዎች የተዘጉ ትምህርት ቤቶች እንዲከፈቱ እየተሰራ መሆኑን የዞኑ ትምህርት መምሪያ አስታወቀ፡፡

በግጭቱበአካባቢያቸው ትምህርታቸውን መከታተል ያልቻሉ ተማሪዎች የዚህ አመት የ10ኛ እና የ12ኛ ክፍል ብሄራዊ መልቀቂያ ተፈታኞች በጎንደር ከተማ ትምህርታቸውን እየተከታተሉ  ነው፡፡

የመምሪያው ኃላፊ አቶ መስፍን እርካቤ ለኢዜአ እንደተናገሩት ግጭቱ በተከሰተባቸው በዞኑ ጭልጋ፣ ምሰራቅና ምእራብ ደንቢያ እንዲሁም በላይ አርማጭሆ ወረዳዎች 117 የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ከህዳር ወር 2011 መግቢያ ጀምሮ ተዘግተው ቆይተዋል።

በተጨማሪም የአይከልና የትክል ድንጋይ ሁለተኛ ደረጃና መሰናዶ ትምህርት ቤቶችም የመማር ማስተማር ሂደታቸው በግጭቱ ተስተጓጉሎ መቆየቱን ገልፀዋል።

በግጭቱ ምክንያት ትምህርት ቤቶቹ በመዘጋታቸው ከ50 ሺህ በላይ ተማሪዎች ትምህርት አቋርጠዋል፡፡

እስካሁን በተደረገው ጥረትም በግጭቱ ከተዘጉት ትምህርት ቤቶች መካከል 14 የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ከታህሳስ ወር መግቢያ ጀምሮ እንዲከፈቱ ተደርገዋል፡፡

በእነዚህ ትምህርት ቤቶች ይማሩ የነበሩ ከ7ሺ በላይ ተማሪዎችንም ወደ ትምህርት ገበታ መመለስ ተችሏል፡፡

በግጭቱ በተዘጉ ሁለት የሁለተኛ ደረጃና የመሰናዶ ትምህርት ቤቶች የሚገኙ 240 የ10ኛና የ12ኛ ክፍል ብሄራዊ መልቀቂያ ተፈታኝ ተማሪዎችም በጎንደር ከተማ በሚገኙ ትምህርት ቤቶች ትምህርታቸውን በመከታተል ላይ ናቸው፡፡

መምሪያው በአሁኑ ወቅት በየወረዳዎቹ የተዘጉ 103 የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤቶችን ስራ ለማስጀመር እንዲቻልም ከአጋር አካላት ጋር በመቀናጀት ትምህርት ቤቶቹ የሚከፈቱበት ሁኔታ በማመቻቸት ላይ ይገኛል፡፡

የሃይማኖት አባቶችና የሀገር ሽማግሌዎች አሁን ላይ እያደረጉት ያለው የሰላምና የእርቅ ተግባራት ለአካባቢዎቹ ሰላምና መረጋጋት ብሎም ለትምህር ቤቶቹ መከፈት ምቹ ሁኔታ እየፈጠረ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የምስራቅ ደንቢያ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ የአለምሰላም ጌጡ በበኩላቸው በወረዳው በግጭቱ ሳቢያ ተዘግተው ከነበሩ 12 የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤቶች መካከል ስምንቱ መከፈታቸውን ገልጸዋል፡፡

ለትምህርት ቤቶቹ መከፈት የህብረተሰቡ፣ የሀገር ሽማግሌዎችና የሃየማኖት አባቶች ሚና ከፍተኛ እንደነበር ተናግረው አራቱን ትምህርት ቤቶች ስራ ለማስጀመር ጥረቱ ተጠናክሮ መቀጠሉን ተናግረዋል፡፡

በጭልጋ ወረዳ በአይከል ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የ10ኛ ክፍል ተማሪ የሆነው አብረሃም ወርቁ በአካባቢው በተፈጠረው የሰላም እጦት ለአንድ ወር ያህል ትምህርት አቋርጦ መቆየቱን ገልጿል፡፡

የ10ኛ ክፍል ብሄራዊ መልቂያ ተፈታኝ በመሆኑ ጎንደር ከተማ በመምጣት በእድገት ፈለግ 2ኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ትምህርቱን እየተከታተል እንደሚገኝ ተናግሯል፡፡

በምሰራቅ ደንቢያ የ12ኛ ክፍል ትምህርቷን ትከታተል የነበረችው ተማሪ ኤልሳቤት ሰለሞን በበኩሏ በመኖሪያ አካባቢዋ በተፈጠረ የጸጥታ ችግር ለሶስት ሳምንት ያህል ትምህርት አቋርጣ ቆይታለች፡፡

ወደ ጎንደር በመምጣትም በአንገረብ የከፍተኛ ትምህርት መሰናዶ ትምህርት ቤት በዚህ ሳምንት ተመዝግባ ትምህርቷን እየተከታተለች መሆኗን ገልፃለች፡፡

የባከኑ የትምህርት ክፍለ ጊዜዎችን ለማካካስም በግሏ ጥረት በማድረግ ላይ እንደሆነች ገልጻለች፡፡ 

በዘንድሮ የትምህርት ዘመን በዞኑ በተደረገው የትምህርት ንቅናቄ ፕሮግራም በአንድ ሺህ 47 የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤቶች 503ሺ ተማሪዎች ተመዝግበው በትምህርት ገበታ ላይ ይገኙ እንደነበር ከመምሪያው የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡