ፍኖተ ካርታው በመምህራን መመልመያ መስፈርት ላይ ትኩረት ሊያደርግ ይገባል - በባህር ዳር የውይይቱ ተሳታፊዎች

83

ባህርዳር  ታህሳስ 24/2011  አዲሱ የትምህርት ፍኖተ ካርታ በአገር አቀፍ ደረጃ ወጥ የሆነ የመምህራን መመልመያ መስፈርት ላይ ትኩረት ሊያደርግ እንደሚገባ የፍኖተ ካርታው ተወያዮች ገለጹ።

በአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ አዘጋጅነት ትናንት በባህር ዳር ከተማ ባለ ድርሻ አካላት በፍኖተ ካርታው ላይ ውይይት ተደርጓል።

ተሳታፊዎቹ በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት ለአገሪቱ የትምህርት ጥራት መጓደል በርካታ ምክንያቶች ቢኖሩም ብቃት ያላቸው መምህራንን በመመደብ ትውልድን መቅረጽ አለመቻል ከፍተኛውን ድርሻ ይይዛል።

በባህር ዳር ከተማ የግል ትምህርት ቤቶች ማህበር ሰብሳቢ መምህር ዘላለም ፀጋ እንደገለጹት ባለፉት አመታት የአገሪቱ የትምህርት ዘርፍ  ከአመራር እስከ መምህር የሚካሂደው ምደባ ለዘርፉ የማይመጥን ነው።

በዚህም የትምህርት አሰጣጥ ስርአቱ በተግባር ያልታገዘና በመረጃ የታጨቀ ንድፈ ሃሳብ  ስለነበረ አብዛኛው የተማረው የሰው ሃይል ስራ ፈጣሪ ከመሆን ይልቅ ጠባቂ እንዲሆን አድርጎታል፡፡

ስለሆነም አዲሱ ፍኖተ ካርታ በመምህራን ምልመላና ስልጠና ላይ ልዩ ትኩረት አድርጎ ካልሰራ በስተቀር ሌሎች ማሸሻያዎችን ቢያደርግም የሚጠበቀውን ያህል ውጤት ላያመጣ ይችላል።

''የአገሪቱን የትምህር ጥራት እንዲወርድ ያደረገው የትምህርት አመራሩ ነው'' ያሉት ደግሞ የአማራ ክልል የሳይንስ ፣ቴክኖሎጂ፣ ኢንፎርሜሽን  ኮሙኒኬሽን ኤጀንሲ የኢንፎርሜሽን መሰረተ ልማት ዳይሬክተር አቶ ጌታቸው ይመር ናቸው፡፡

የትምህርት ጥራት እንዲጠበቅ ለመምህራን በርቀትና በክረምት የሚሰጥ የደረጃ ማሻሻያ ትምህርት ሊፈተሽ ይገባዋል።

አዲሱ የትምህርት ፍኖተ ካርታም በውጤታቸው የተሻሉ መምህራንን ወጥ በሆነ አገራዊ መስፈርት ከመቅረጽ  በተጨማሪ የርቀትና የክረምት ትምህርቶችን ማስቀረት ይኖርበታል።

አዲሱን የትምህርት ፍኖተ ካርታ ለውይይት ያቀረቡት የክልሉ ትምህርት ቢሮ ሃላፊ ዶክተር ይልቃል ከፋለ በበኩላቸው የአዲሱን ፍኖተ ካርታ አሁን ለሚስተዋለው የትምህርት ጥራት መጓደል ብቁ መምህራንን አለመመደብ አንዱና ዋነኛው እንደሆነ በመረጋገጡ በጉዳዩ ላይ ልዩ ትኩረት የሰጠ ነው ።

አዲሱ ፍኖተ ካርታ ከ12 ኛ ክፍል የተሻለ ውጤት ያመጡና ለሙያው ልዩ ፍላጎት ያላቸውን መምህራን እንዲሰለጥኑ የሚያስችል ነው።

አንድ ወጥ የሆነ አገራዊ መስፈርትን መሰረት ያደረገ  መመልመያ  ከማዘጋጀት ባለፈ ሙያው በዩኒቨርሲቲ ደረጃ  እንደሌሎቹ ሙያዎች በመደበኛ የስልጠና አሰጣጥ እንዲሰጥ ይደረጋል።

በባህር ዳር ከተማ ሙሉዓለም አዳራሽ ትናንት ለግማሽ ቀን በተካሄደው የውይይት መድረኩ ላይ የመንግስት የስራ ሃላፊዎች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ በተለያየ ደረጃ የሚገኙ የክልሉ የዘርፉ አመራሮች ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም