ቤተ ክርስቲያኗ ያዘጋጀችው የሰላም ኮንፈረንስ በአምቦ ከተማ ተጀመረ

70

አምቦ ታህሳስ 24/2011 በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን የምእራብ ሸዋ ዞን ሃገረ ስብከት የተዘጋጀና ሰላምና ሀገራዊ መግባባትን ዓላማ ያደረገ የሦስት ቀናት ኮንፈረንስ ዛሬ በአምቦ ከተማ ተጀመረ።

በኮንፈረንሱ መክፈቻ ላይ  ተገኝተው ንግግር ያደረጉት የሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጻጻስ ብጹህ አቡነ ኤጺፋንዮስ እንደገለጹት ቤተክርሲቲያኗ የሕዝቦችን ሰላምና አንድነት ከማስጠበቅ ረግድ ለበርካታ ዓመታት ከፍተኛ ሚና ስትጫወት ቆይታለች፡፡

በአሁኑ ጊዜም ቤተክርስቲያኗ የሰላም አምባሳደርነት ተግባሯን በመወጣት በተለያዩ ቤተ እምነቶች ስለ ሰላም አስፈላጊነትና ጠቀሜታ በልዩ ትኩረት ህዝቡን በማስገንዘብ ላይ መሆኗን ገልጸዋል፡፡

" የሀገሪቱ ሰላም ተጠብቆ በህዝቦች ዘንድም ብሔራዊ መግባባት ተፈጥሮ ማየት የቤተክርስቲያኗ ዋነኛ ዓላማ ነው " ያሉት ሊቀ ጻጻሱ የእምነት አባቶችም በአካባቢያቸው በሚገኙ ህዝቦች ዘንድ መግባባት እንዲፈጠር ከምን ጊዜውም በላይ በትኩረት መስራት እንዳለባቸው አስገንዝበዋል፡፡

''ወጣቶች ከስሜታዊነት ወጥተው በምክንያታዊነት እንዲመሩ ከማድረግ አንጻር የእምነት አባቶች ተሰሚነታቸውን በመጠቀም መምከርና መገሰጽ ይኖርባቸዋል'' ያሉት ደግሞ የምዕራብ ሸዋ ዞን ሀገረ ስብከት ዋና ስራ አስኪያጅ ሊቀ ትጉሃን ያሬድ አበበ ናቸው፡፡ 

''ሰላም ከሌለ ወጥቶ ከመግባት ጀምሮ በነጻነት ማምለክም አይቻልምና ሁሉም በየደረጃው የሚገኝ ህብረተሰብ ስለ ሰላም መጠበቅና ሀገራዊ አንድነት ከቤተክርስቲያን ጎን መቆም ይኖርበታል'' ሲሉም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

ለሶስት ቀናት በሚካሄደው ኮንፈረንስ  ላይ የቤተክርስቲያኗ የእምነት አባቶች፣ የሀገር ሽግሌዎች፣ ወጣቶችና የመንግስት የስራ ኃላፊዎች ተሳታፊ ሆነዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም