ወልዋሎ አዲግራት ዩንቨርስቲ ከፋሲል ከተማ እሁድ በአዲግራት ስታዲየም ሊጫወቱ ነው

93

አዲስ አበባ ታህሳስ 24/2011 በአማራና በትግራይ ክልል እግር ኳስ ክለቦች መካከል የሚደረገው የፕሪሚየር ሊግ ጨዋታ ከአንድ ዓመት በኋላ በሜዳቸው ሊከናወን መሆኑን የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን አስታወቀ።

በፕሪሚየር ሊጉ ዘጠነኛ ሳምንት እሁድ ታህሳስ 28 ቀን 2011 ዓ.ም በአዲግራት ስታዲየም ወልዋሎ አዲግራት ዩንቨርስቲ ከፋሲል ከተማ ከቀኑ ዘጠኝ ሰዓት ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።

ህዳር 9 ቀን 2010 ዓ.ም በሁለቱ ክልሎች ክለቦች መካለል የተደረጉ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ጨዋታዎች ላይ በደጋፊዎች መካከል በተነሳው ረብሻ ምክንያት የሁለቱ ክልል ክለቦች ጨዋታ በአዲስ አበባ ስታዲየም መደረጋቸው ይታወሳል።

በዚህም ምክንያት የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የአማራና የትግራይ ክልል ክለቦች በገለልተኛ ሜዳ እንዲጫወቱ በመወሰን በ2010 ዓ.ም የነበሩ የሁለቱ ክልል ክለቦች ጨዋታ በአዲስ አበባ ስታዲየም መደረጋቸው ይታወሳል።

ክለቦቹና በገለልተኛ ሜዳ በመጫወታቸው በሜዳቸው ሊያገኙት የሚችሉትን ጥቅም ስላሳጣቸው በተደጋጋሚ ጊዜ ለእግር ኳስ ፌዴሬሽኑ በተደጋጋሚ ቅሬታ ሲያቀርቡ ቆይተዋል።

በተያዘው የውድድር ዓመት በፕሪሚየር ሊጉ የሁለቱ ክልል ክለቦች እርስ በእርስ ሲገናኙ ጨዋታቸውን በሜዳቸው የማድረግ ጉዳይ መፍትሔ ያላገኘ ጉዳይ ሆኖ ቆይቷል።

በዚህም ምክንያት የሁለቱም ክልሉ ክለቦች ከአንድ ዓመት በላይ እርስ በእርስ የሚያደርጉትን ጨዋታ በሜዳቸው ማድረግ አልቻሉም።

ታህሳስ 4 ቀን 2011 ዓ.ም በአዲስ አበባ በተደረገው ስብስባ የትግራይና አማራ ክልል ክለቦች የእርስ በርስ ጨዋታዎቻቸውን በየሜዳቸው ለማድረግ ተስማምተው ነበር።

በስብሰባ የባህል እና ቱሪዝም ሚኒስትር ዶክተር ሂሩት ካሳው፣ የስፖርት ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ርስቱ ይርዳ፣ የሁለቱ ክልሎች ክለብ ተወካዮች፣ የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን አመራሮችና የጸጥታ አካላት ተገኝተውበትም ነበር።

ክለቦቹና ክልሎቹ እንደተስማሙ ቢገለጽም በስምምነቱ ወቅት ይደረጋሉ የተባሉ ጨዋታዎች በድጋሚ መራዘም ጉዳዩ እልባት እንዳለገኘ ያመላከተ ነበር ማለት ይቻላል።

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የአማራ እና የትግራይ ክልል ከፍተኛ አመራሮች፣ ስፖርት ኮሚሽኖች፣ እግር ኳስ ፌዴሬሽኖች እና ክለቦች በየክልላቸው ችግሮችን መፍታት በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ መክረዋል። በዚህም መሰረት:-

1ኛ. ለተለያዩ ደጋፊ ማህበራት እና ደጋፊዎች እንዲሁም በሁለቱም ክልሎች ለሚገኙ የተለያዩ መገናኛ ብዙሃን ጉዳዩን አስመልክቶ ስለተሰሩ ሥራዎች ጋዜጣዊ መግለጫዎችን የሰጡ መሆናቸውን፣

2ኛ. በየደረጃው ለሚገኙ የስፖርት ተቋማት እና ባለሙያዎች የግንዛቤ ማስጨበጫ መስጠታቸውን እና የቤት ሥራቸውን ማጠናቀቃቸውን   ለኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ማሳወቃቸውን አስታውቋል።

በውድድሩ ኘሮግራም መሠረት በየክልሉ በመሄድ ጨዋታዎቻቸውን እንደሚያካሂዱ፣ እንግዳውን ቡድን በደማቅ ሁኔታ በመቀበል እና ተገቢውን መስተንግዶ በማድረግ ከጨዋታውም በኋላ በክብር እንደሚሸኑ መስማማታቸውን በደብዳቤ መግለጻቸውንም ጠቅሷል።

እግር ፌዴሬሽንና የሊግ ኮሚቴ ክልሎቹ ያቀረቡትን በጎ ሃሳብ መሠረት በማድረግ መደበኛ የኘሪሚየር ሊጉ ውድድሮች በወጣላቸው ኘሮግራም መሠረት እንደሚቀጥሉና የተስተካካይ ጨዋታዎቹን ኘሮግራም ቀጣይነት በቅርብ ጊዜያት በማውጣት የሚያሳውቅ መሆኑን ገልጿል።

በዚሁ መሰረት እሁድ ታህሳስ 28 ቀን 2011 ዓ.ም ወልዋሎ አዲግራት ዩንቨርስቲ ከፋሲል ከተማ በአዲግራት ስታዲየም ጨዋታቸውን የሚያደርጉ ይሆናል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም