ለበዓሉ የመሰረታዊ ሸቀጦች እጥረት እንዳይኖር ቅድመ ዝግጅት ተደርጋጓል-አቶ መስፍን አሰፋ

1358

አዲስ አበባ ታህሳስ 24/2011 ለበዓሉ የመሰረታዊ ሸቀጦች እጥረትና  ምክንያታዊ ያልሆነ የዋጋ ጭማሪ እንዳይኖር ከወዲሁ ቅድመ ዝግጅት ማድረጉን የአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ አስታወቀ።

ቢሮው ከከተማው ሸማቾች ህብረት ስራ ማህበር ጋር በመተባበር ለበዓሉ የተደረጉ ዝግጅቶችን አስመልክቶ ዛሬ መግለጫ ሰጥቷል።

በመግለጫው ወቅት የቢሮው ምክትል ሃላፊ አቶ መስፍን አሰፋ እንዳሉት በበዓሉ ወቅት አለአግባብ የዋጋ ጭማሪና የሸቀጦች እጥረት እንዳይኖር ቢሮው ከባለድርሻ አካላት ጋር እየሰራ ነው።

ከአማራ፣ ኦሮሚያ፣ ከደቡብ ክሌሎች ካሉ አምራቾች ጋር በመተባባር የሽንኩርትና የሌሎች መሰረታዊ የሸቀጣ ሸቀጥ ምርቶች በብዛት በመግዛት ለህብረተሰቡ እንዲቀርብ እየተደረገ መሆኑንም ገልጸዋል።

እነዚህን የግብርናና የኢንዱስትሪ ምርቶችን በስምንት ክፍለ ከተሞች  ባዛሮችን በመክፈትና በመሰረታዊ የሸማቾች ህብረት ስራ ማህበራት  ምርቶችን ለማቅረብ መዘጋጀታቸውንም ጠቁመዋል።

በዘንድሮ በዓልም ከወትሮ በተለየ ለህብረተሰቡ በጥራትና በቅናሽ ዋጋ ለማድረስ በተወሰኑ ክፍለ ከተሞች ተወስኖ የነበረውን የባዛርና ኤግዚቢሽን ስራ በአብዛኞቹ ክፍለ ከተሞች እንዲካሄዱ ተደርጓል ብለዋል።

በ144 የሸማቾች ህብረት ስራ ማህበራትም ለ28 ሺህ ቸርቻሪ ነጋዴዎች ምርቶቹ እንዲዳረሱ በማድረግ አላግባብ ጭማሪና  የደላላ ጣልቃ ገብነት እንዳይኖር ለማድረግ ግብረ ሃይል ተቋቁሞ እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።

የከተማው ህብረት ስራ ማህበራት ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር  አቶ ግዛቸው አሊ በበኩላቸው ለበዓሉ  ከመደበኛው የዘይት አቅርቦት በተጨማሪ ከ220 ሺህ ሊትር በላይ ዘይትና 10 ሺህ 800 ኪሎ ቅቤ በህብረት ስራ ማህበራት ቀርቧል።

ለበዓሉ እስከ 20 ሺህ ኩንታል ሽንኩት ለማስገባት የታቀደ ሲሆን እስከ ትላንትና ድረስ አራት ሺህ ኩንታል ሽንኩርት ለገበያ መቅረቡን አስታውሰዋል።

የመሰረታዊ ሸቀጥ አቅርቦት እንዳይስተጓጎል ከክልል አምራቾች ጋር የገበያ ትስስር ተፈጥሯል።

ሸማቹም የዱቄት፣ የበርበሬ፣  የሽንኩርት፣ የዶሮ፣ የቅቤና ሌሎች ምርቶችን መንግስት በተመጣጣኝ ዋጋ ማቅረቡን ተረድቶ በበዓል ወቅት ከሚደረግ አላስፈላጊ የዋጋ ጭማሪ እራሱን እንዲጠብቅ አሳስበዋል።

ማህበረሰቡ በገበያ ወቅት ለሚገጥመው ችግርም 8588 ነጻ የስልክ መስመር ደውሎ እንዲያሳውቅ ጠይቀዋል።