የተጀመረውን ለውጥ ስኬታማ ለማድረግ ለገለልተኛ ተዓማኒና ጠንካራ ተቋማት ግንባታ ትኩረት ይሰጣል- ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ

113

አዲስ አበባ ታህሳስ24/2011 መንግስት የጀመረውን ለውጥ ስኬታማ ለማድረግ ለገለልተኛ ተዓማኒና ጠንካራ ተቋማት ግንባታ ትኩረት እንደሚሰጥ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር  ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ ገለጹ።

ሚኒስትሩ ይህንን ያሉት የስራ ጊዜያቸውን የጨረሱትን በኢትዮጵያ የእንግሊዝ አምባሳደር ሱዛና ሞርሄድ ዛሬ በጽህፈት ቤታቸው በሸኙበት ወቅት ነው።

በአጠቃላይ ለውጡን ስኬታማ ለማድረግ ለገለልተኛ ተዓማኒና ጠንካራ ተቋማት ግንባታ ትኩረት እንደሚስጥ ለተሰናቧቿ አምባሳደር መግለጻቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽህፈት ቤት ለኢዜአ በላከው መግለጫ አስታውቋል።

እንግሊዝን ጨምሮ ዓለም አቀፍ ማህበረሰብ ይህን የለውጥ ስራ እንዲደግፉም ጥሪ አቅርበዋል።

በኢትዮጵያና እንግሊዝ መሐከል ያለው ግንኙነት ረዥም ዕድሜ ያስቆጠረ መሆኑን ዶክተር ወርቅነህ አስታውሰው እንግሊዝ የሚጨበጥ እና ውጤታማ ድጋፍ ስታደርግ መቆየቷን ተናግረዋል፡፡

ተሰናባቿ አምባሳደር ሱዛና ሞርሄድ በበኩላቸው ኢትዮጵያ ለውጥ ላይ ባለችበት ወቅት በመስራታቸው እንደሚደሰቱ ተናግረዋል።

የእንግሊዝ መንግስት በተቋማት ግንባታ፣ በስራ ዕድል ፈጠራ እና በሌሎችም መስኮች ድጋፍ ለማድረግ ፍላጎት እንዳለውም ገልጸዋል።

ኢትዮጵያና እንግሊዝ የዲፕሎማሲ ግንኙነታቸውን በይፋ የጀመሩት እ.ኤ.አ. 1897 መሆኑን ከቃል አቀባይ ጽህፈት ቤቱ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

የእንግሊዝ የአፍሪካ ጉዳዮች ሚኒስትር ዴኤታ ሚስ ሀሪዬት ባልድዊን በህዳር ወር 2011 ዓ.ም በኢትዮጵያ ጉብኝት ያደረጉ ሲሆን በቆይታቸውም ከውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ሂሩት ዘመነ ጋር ሁለቱ አገራት ያላቸውን ትብብር ማስፋት በሚችሉባቸው ጉዳዮች ላይ መወያየታቸው ይታወሳል።

በውይይቱ ላይ እያደገ የመጣው የአገራቱ የንግድና ኢንቨስትመንት ትብብር ይበልጥ ማሳደግ እንደሚገባም የጋራ መግባባት ላይ መድረሳቸውም ይታወቃል።

የኢትዮጵያና እንግሊዝ የንግድ ልውውጥ መጠን 2 ቢሊዮን ዶላር መድረሱን መረጃዎች ያመለክታሉ።

ሁለቱ አገራት በንግድ፣ በትምህርት፣ በባህል፣ በስደተኞች ጉዳይና በልማት ትብብር ላይ ጠንካራ ግንኙነት ያላቸው ሲሆን በተለይም በልማቱ መስክ  በእንግሊዝ ዓለም አቀፍ የእርዳታ ድርጅት (ዲ ኤፍ አይ ዲ) በኩል ለልማት ስራዎች የፋይናንስ ድጋፍ ታደርጋለች።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም