በሐረር ከተማ የተገነቡ መሰረተ ልማቶች ተገቢውን አገልግሎት እየሰጡ አይደለም -ነዋሪዎች

58

ሀረር ታህሳስ23/2011 በሐረር ከተማ ባለፉት ዓመታት ተገንብተው ለአገልግሎት ከበቁ መሰረተ ልማቶች አብዛኞቹ በብልሽት ምክንያት ተገቢውን አገልግሎት እየሰጡ አይደለም ሲሉ ነዋሪዎች ቅሬታቸውን አቀረቡ።

ችግሮቹ ከአሰራር ክፍተትና ከክትትል ማነስ የመጡ መሆናቸውን የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ገልጸዋል።

የክልሉ ነዋሪዎችና ባለድርሻ አካላት የከተማው መሰረተ ልማት ግንባታዎችን አስመልክቶ ከክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ጋር ተወያይተዋል።

ነዋሪዎቹ በመድረኩ ላይ እንደገለጹት በከተማው ማዘጋጃ ቤት ባለፉት ዓመታት ተገንብተው ለአገልግሎት የበቁት ብዙዎቹ መሰረተ ልማቶች በአጭር ጊዜ ውስጥ ለብልሸት ተዳርገዋል።

የጥርብ ድንጋይ መንገድ፣ የህዝብ መጸዳጃ ቤቶች እንዲሁም የጎርፍና ፍሳሽ መውረጃ ትቦዎች ተመርቀው ብዙ ሳያገለግሉ ለብልሽት እየታዳረጉ መሆናቸውን ነው ነዋሪዎቹ የገለጹት።

የአሚር ኑር ወረዳ ነዋሪ አቶ እንዳለ ኃይለሚካኤል በበኩላቸው ባለፉት ዓመታት በከተማው የተከናወኑት የመንገድና የፍሳሽ ውሃ መውረጃዎች  በመፈራረሳቸው በተለይ በዝናብ ወቅት ለችግር እየተዳረጉ መሆናቸውን ገልጸዋል።

"የሚመለከተው የመንግስት አካልም ሆነ መሀንዲሶች ወደታች ወርደው የማስተካከያ ሥራዎችን ለመስራት ሲንቀሳቀሱ እይታይም፤ ይህ ደግሞ በነዋሪዎች ላይ ቅሬታ እያሳደረብን ነው" ብለዋል።

"በከተማው የሚገነቡት መንገዶች ከኪራይ ሰብሳቢነት ጋር በተያየዘ የጥራት ችግር ስለሚስተዋልባቸው ለነዋሪዎችና ለተሽከርካሪዎች ምቹ አገልግሎት እየሰጡ አይደለም" ሲሉ የገለጹት ደግሞ የሐኪም ወረዳ ነዋሪ አቶ ታረቀኝ ጋሮማናቸው።

በመንገድ ግንባታ ወቅት ከመሀንዲስ ጀምሮ እስከ ማህበራትና ቢሮ አመራር ድረስ በጥቅም የመተሳሰር ሁኔታ ስለሚስተዋል አሰራሩ እንዲፈተሽ ጠይቀዋል።

አቶ ኤፍሬም ኡንታና የተባሉ ነዋሪ በበኩላቸው "የግንባታ ሥራዎቹ ለብልሽት እየተዳረጉ ያሉት ጥቃቅንና አነስተኛ ማህበራት በቂ ስልጠናና አቅም ሳይኖራቸው ስራውን እንዲሰሩ በመደረጉ ነው" ብለዋል።

እንደ አቶ ኤፍሬም ገለጻ፣ በክልሉ በአብዛኛው ፍትሃዊ አሰራርን ከመከተል ይልቅ በወገንተኝነት የተመረጡ ውስን ማህበራት ብቻ በመሰረተ ልማት ግንባታ ሥራ ላይ እንዲሳተፉ መደረጉ በሥራው ላይ የጥራት ችግር እንዲከሰት አድርጓል።

አዲሱ የክልሉ አመራሮች በቀጣይ በሚሰሩ የመሰረተ ልማት ሥራዎች ላይ መሰል ችግሮች እንዳይከሰቱ ጥንቃቄ እንዲደረግም ጠይቀዋል።

የከተማው ማዘጋጃ ቤት ሹም አቶ አሪፍ መሀመድ በከተማው ባለፉት 4 ዓመታት 111 ኪሎ ሜትር የውስጥ ለውስጥ ጥርብ ድንጋይ መንገድ፣ የውሃ መውረጃ ትቦና የዘጠኝ አነስተኛ ድልድዮች ግንባታ ሥራዎች መከናወናቸውን ገልጸዋል።

በግንባታ ሥራዎቹ ላይ ከነዋሪው የተነሱት ቅሬታዎች ተገቢ መሆናቸውን አምነው ለጥራት መንስኤ የሆኑ ጉዳዮችን ለማጣራትና ለማረም በአሁኑ ወቅት የተለያዩ የአደረጃጀት ስራዎች እየተከናወኑ መሆናቸውንና ዘንድሮም ችግሮችን ለመፍታት ርብርብ እንደሚደረግ አመልክተዋል።

የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኦርዲን በድሪ በበኩላቸው ከተሳታፊው ለተነሳው ጥያቄ ምላሽ በሰጡበት ወቅት እንዳሉት ችግሩ የተፈጠረው በአሰራር ክፍተትና በክትትል ማነስ ነው።

በአሁኑ ወቅት ሁኔታውን ለማጣራት እየተሰራ መሆኑንም አመልክተዋል።

በተለይ በዘንድሮ በጀት ዓመት 2 ሺህ ወጣቶችን የሥራ ዕድል ተጠቃሚ የሚያደርጉና ከ206 ሚሊዮን ብር በሚበልጥ በጀት በሚገነቡ የመሰረተ ልማት ስራዎች ላይ ያለፉት ስህተቶች እንዳይደገሙ ከሁሉም ተቋማትና ወረዳዎች ጋር በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም