በአዲስ አበባ ቦሌ አራብሳ የባለ 7 ፎቅ ኮንዶሚኒየም ነዋሪዎች የጋራ መጠቀሚያ ህንጻ አልተገነባልንም አሉ

238

አዲስ አበባ ታህሳስ 23/2011 በአዲስ አበባ ቦሌ አራብሳ የባለ 7 ፎቅ ኮንዶሚኒየም ነዋሪዎች የጋራ መጠቀሚያ ህንጻ ሳይገነባልን ክፍያ መፈጸማችን ተገቢ አይደለም አሉ፡፡

የአስተዳደሩ ቤቶች ልማት ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት በበኩሉ ግንባታው ያልተከናወነው መጀመሪያውኑ በዲዛይን ባለመካተቱ ነው ብሏል፡፡

በአዲስ አበባ ከተማ ቦሌ አራብሳ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ የጋራ መኖሪያ ቤቶች ግንባታ የተከናወነው ጨርቆስ፣ ልደታና ፕሮጀክት አስራ አምስት በተሰኙ በሶስት ፕሮጀክቶች ተከፋፍሎ ነው፡፡

በሳይቱ አጠቃላይ ባለ 10/90 እና 20/80 ፕሮግራም መሰረት በባለ ሁለት፣ ባለ አራትና ባለ 7 ፎቆች የተገነቡ 20 ሺህ 227 ቤቶች ለእድለኞች በዕጣ ተላልፈዋል፡፡

እጣው ወጥቶላቸው ቤቱን የተረከቡ ሁሉም የቤት እድለኞችም ከዋናው መኖሪያ ቤታቸው በተጨማሪ የተለያዩ ማህበራዊ  ጉዳዮቻቸውን ለሚያከናውኑባቸው የጋራ መጠቀሚያ /ኮሚናል/ ለሚባሉት ህንጻዎችም ክፍያ የፈጸሙ ናቸው፡፡

ከሰሞኑ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ኤጀንሲ ቅሬታ ያቀረቡት የባለ ሰባት ፎቅ የጋራ መኖሪያ ቤት ነዋሪዎች ታዲያ እንደማንኛውም የቤት እድለኛ ከተረከብነው መኖሪያ ቤታችን  በተጨማሪ ለጋራ መጠቀሚያ ህንጻ /ኮሚናል/  ክፍያ መፈጸማቸውን ይገልጻሉ።

ይሁን እንጂ በባለ 2 ፎቅና ባለ አራት ፎቅ ህንጻዎች ላይ ቤት የደረሳቸው  የ10/90 እና  የ20/80 ቤት እድለኞች  የጋራ መገልገያ  ህንጻ ተጠቃሚ ሲሆኑ ባለ 7 ፎቆች ላይ የቤት እጣ ለደረሰን ነዋሪዎች ተለይቶ  የጋራ መጠቀሚያ ያለመገንባቱ  ቅሬታ ውስጥ ከቶናል ይላሉ ቅሬታ አቅራቢዎቹ፡፡

ቅሬታ አቅራቢዎቹ ሃዘንም ሆነ ሌሎች ማህበራዊ ግንኙነቶቻውን በአግባቡ እንዳይፈጽሙ የጋራ መጠቀሚያ ህንጻዎች አለመኖር ተጽዕኖ እንዳሳደረሰባቸው ነው የሚናገሩት፡፡

የአዲስ አበባ ቤቶች ልማት ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት በሰጠው ምላሽም የጋራ መጠቀሚያ ህንጻዎችን ግንባታ ያከናወንኩት የመኖሪያ ህንጻዎቹን ተጨባጭ ሁኔታ ታሳቢ በማድረግ  ነው ይላል፡፡

በፕሮጀክት ጽሕፈት ቤቱ ምክትል ስራ አስኪያጅ ኢንጂነር ተክሉ ፍቅሩ እንደሚናገሩት ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤቱ ግንባታዎች ሲካሄዱ ቀድሞ የተዘጋጀውን ዲዛይን መሰረት በማድረግ እንጂ ከዲዛይን ውጪ የተጨመረም ሆነ የተቀነሰ  የጋራ መጠቀሚያ ህንጻ የለም ፡፡

በፕሮጀክት ጽሕፈት ቤቱ መሃንዲስ የሆኑት ጎይቶም በርሄም የግንባታ ዲዛይኑን መሰረት አድርገው እንዳስረዱት በቦሌ አራብሳ የተገነቡት ሁሉም ባለ ሰባት ፎቅ የጋራ መኖሪያ ቤቶች የጋራ መጠቀሚያ ህንጻ ግንባታ አልተካሄደላቸውም ብለዋል፡፡

ነዋሪዎቹም  መንግስት ግንባታውን እንዲያከናውንላቸው በመጠየቅ፤ ይህ የማይሆን ከሆነ ደግሞ የከፈሉት ገንዘብ ተመላሽ እንዲሆንላቸው ጠይቀዋል፡፡

በጉዳዩ ላይ ምላሽ ለማግኘት የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ኤጀንሲ ለአዲስ አበባ ቤቶች አስተዳደር ኤጀንሲ ስራ አስኪያጅና ለቤቶች ልማትና አስተዳደር ቢሮ ኃላፊ ጥያቄውን በተደጋጋሚ በአካልና በስልክ አቅርቧል፡፡

ሆኖም ነዋሪዎቹ ላነሱት ቅሬታና ጥያቄ  ከኤጀንሲው፣ ከቢሮውና ከፕሮጀክት ጽሕፈት ቤቱ የተቋቋመ የጋራ ኮሚቴ ተወያይቶ ጉዳዩን በሚገባ ካጠራ በኋላ ምላሽ እንሰጣለን ብለዋል ፡፡

 ለአሁኑ ግን እንዲህ ነው የሚል ምላሽ መስጠት አንፈልግም የሚል ምላሽም ሰጥተዋል፡፡

ከአዲስ አበባ ቤቶች ግንባታ ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት ያገኘነው መረጃ እንዳመለከተው በቦሌ አራብሳ ፕሮጀክት 15 ከተገነቡት 248 ህንጻዎች መካከል 16 ባለ ሰባት ፎቅ ፣ በጨርቆስ ግንባታ ፕሮጀክት ከተገነቡት 256 ህንጻዎች መካከል 9ኙ ባለ ሰባት ፎቅ እንዲሁም በልደታ ፕሮጀክት ከተገነቡት 171 ብሎኮች መካከል 23 ህንጻዎች ባለ 7 ፎቅ ናቸው፡፡

በግንባታ ዲዛይኑ መሰረትም 48 ባለሰባት ፎቅ ህንጻዎች የጋራ መጠቀሚያ ህንጻ አልተገነባላቸውም፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም