የመማሪያ ክፍል መጨናነቅ ተማሪዎችን ለመከታተል ተግዳሮት ሆኖብናል — የባህር ዳር መምህራን

1113

ባህር ዳር ታህሳስ 23/2011 በባህር ዳር ከተማ አስተዳደር እስከ 100 ህጻናት በአንድ ክፍል ውስጥ ተጨናንቀው መማራቸው ተማሪዎቹን ተከታትሎ ለማብቃት እንቅፋት እንደሆነባቸው የቅደመ መደበኛ ትምህርት አመቻች መምህራን ተናገሩ።

በከተማ አስተዳደሩ በሚገኙ 36 የመንግስት ትምህርት ቤቶች 3 ሺህ 583 ህጻናት ተመዝግበው የቅድመ መደበኛ ትምህርት እየተከታተሉ መሆናቸውም ተመልክቷል።

በሽምብጥ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የቅድመ መደበኛ ትምህርት አመቻች መምህርት የሻረግ ጋውን ለኢዜአ እንዳሉት በአንድ ክፍል ውስጥ የተማሪ ቁጥር ከ40 መብለጥ የለበትም።

“ይሁን እንጂ በክፍል ጥበት ምክንያት ስድስት ዓመት የሞላቸውን ከ100 የሚበልጡ ህጻናት በአንድ ክፍል ውስጥ ለማስተማር ተገደናል፤ ይህም የህጻናቱን ክፍተት ለይቶ ለማብቃት አስቸግሮናል” ብለዋል።

በየካቲት 23 የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት የቅድመ መደበኛ ትምህርት አመቻች መምህርት ሙሉነሽ ተባባል በበኩላቸው ዕድሜያቸው ከአራት እስከ ስድስት ዓመት የሆናቸው 78 ህፃናት በአንድ ክፍል ውስጥ እየተማሩ መሆናቸውን ገልጸዋል።

በአንድ ክፍል ውስጥ የህጻናቱ ቁጥር ከሚፈለገው በላይ ከመሆኑ በተጨማሪ እንደዕድሜያቸው ለይቶ ትምህርቱን በጨዋታ መልክ  በቀላሉ ለማስተማር መቸገራቸውንም ተናግረዋል።

“ህጻናቱ በዕድሜያቸው ተለይተው የሚማሩበት ምቹ ሁኔታ ቢፈጠር በየደረጃቸው ማወቅ የሚገባቸውን አውቀው እንዲወጡ ያግዛል” ብለዋል።

የሽምብጥ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ርዕሰ መምህር አቶ ገብሬ ይግዛው በበኩላቸው የትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅ ከ2008 ዓ.ም ጀምሮ የቅድመ መደበኛ ትምህርት  እየተሰጠ መሆኑን ገልጸዋል።   

የህጻናቱ ቁጥር ከተጠበቀው በላይ እየጨመረ በመምጣቱ ሦስት ክፍሎችን በቆርቆሮ በመስራት ከአራት እስከ ስድስት ዓመት ያሉ 312 ህጻናትን ተቀብለው በማስተማር ላይ መሆናቸውን ተናግረዋል።

በአንድ ክፍል ውስጥ ህጻናት ከሚገባው ቁጥር በላይ ተጨናንቀው እንዲማሩ መደረጉን የጠቀሱት አቶ ገብሬ ችግሩን ለመፍታት በቀጣዩ ወር የ1ኛ ደረጃ ተማሪዎች አዲስ ወደ ተገነባው መማሪያ ክፍል የሚዛወሩ መሆኑን አመልክተዋል።

ሁለት የልጅ ልጆቻቸውን በማስተማር ላይ መሆናቸውን የተናገሩት ወይዘሮ አለሚቱ ዘውዱ በበኩላቸው ” የቅድመ መደበኛ ትምህርት በአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች መጀመሩ በግል ከፍሎ ለማስተማር አቅም ለሌለን ወላጆች ጥሩ አጋጣሚ ፈጥሯል” ብለዋል።

ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ህጻናት በአንድ ክፍል ውስጥ ተጨናንቀው እየተማሩ ስለመሆኑ መታዘባቸውን የገለጹት ወይዘሮ አለሚቱ፣ ይህም ለተማሪዎች በቂ እውቀት ለማስጨበጥና ሁሉንም ተከታትሎ ለመደገፍ እንቅፋት እንደሚሆን ነው የተናገሩት።

የክልሉ መንግስት ችግሩን ለመፍታት ተጨማሪ መማሪያ ክፍሎችንና ትምህርት ቤቶችን እንዲገነባም ጠይቀዋል ።

የባህር ዳር ከተማ አስተዳደር ትምህርት መምሪያ ኃላፊ አቶ ሙሏለም አቤ በበኩላቸው በመንግስት የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤቶች 3 ሺህ 583 ህጻናት የቅድመ መደበኛ ትምህርታቸውን እየተከታተሉ መሆናቸውን ገልጸዋል።

“በበጀት እጥረትና በማህበረሰቡ ግንዛቤ ማነስ ምክንያት ተጨማሪ ክፍሎችን መገንባት ባለመቻሉ ብዛት ያላቸው ተማሪዎች በአንድ ክፍል ውስጥ ተጣበው ለመማር ተገደዋል” ብለዋል።

ችግሩን ለመፍታት የከተማ አስተዳደሩ በጀት እንዲመድብ መምሪያው በተደጋጋሚ ጥያቄ እያቀረበ መሆኑን ጠቁመው፣ የሕብረተሰቡን ግንዛቤና ተሳትፎ በማሳደግም ተጨማሪ መማሪያ ክፍሎችን በመገንባት ችግሩን ለመፍታት እንደሚሰራ አስረድተዋል።

በክልሉ በዘንድሮው የትምህርት ዘመን ከ723 ሺህ የሚበልጡ ህጻናት ተመዝግበው የቅድመ መደበኛ ትምህርት በመከታተል ላይ መሆናቸው ታውቋል።