ለከተማዋ ልማትና እድገት መፋጠን የበኩላችንን እንወጣለን - የጋምቤላ ከተማ ነዋሪዎች

72

ጋምቤላ ታህሳስ 23/2011 የአካባቢያቸውን ሰላም በማስጠበቅ ለከተማዋ ልማትና እድገት መፋጠን የበኩላቸውን እንደሚወጡ የጋምቤላ ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ፡፡

ነዋሪዎቹ አልፎ አልፎ የሚታዩ የሰላም ችግሮችን በመፍታት የከተማዋን እድገት ማፋጠን በሚቻልባቸው ጉዳዮች ዙሪያ ትናንት ከክልሉ ርዕሰ መስተዳደር አቶ ኡሞድ ኡጁሉ ጋር ውይይት አድርገዋል፡፡

በውይይቱ ላይ የተገኙ አንዳንድ የከተማዋ ነዋሪዎች እንዳሉት የከተማዋን ሰላም ለማስጠበቅ ከመንግስት ጎን በመሆን ይሰራሉ፡፡

ከነዋሪዎች መካከል ወይዘሮ ኑኑ ኡጉድ በሰጡት አስተያየት እርስ በእርስ የነበራቸውን የአንድነት፣ የፍቅርና የአብሮነት ባህል በማጎልበት ለከተማዋ እድገት መፋጠን የበኩላቸውን እንደሚወጡ  ተናግረዋል፡፡

የከተማዋን ሰላም ዘላቂ ለማድረግ የክልሉ መንግስት በህዝቡ የሚነሱ የመልካም አስተዳደርና የልማት ጥያቄዎችን ለመመለስ ትኩረት ሊያደርግ እንደሚገባ ጠይቀዋል፡፡

የአመራር አካላቱም ለለውጥ ዝግጁ መሆን እንዳለባቸው የጠየቁት ወይዘሮ ኑኑ ለከተማዋ እድገት መፋጠን ከአመራሩ ጎን በመሆን ለመስራት ዝግጁነታቸውን  አረጋግጠዋል፡፡

''ለከተማችን ሰላም መስፈንና እድገቷን በተሻለ ደረጃ ለማስቀጠል እያንዳንዱ የከተማዋ ህዝብ በጋራ መስራት አለበት'' ያሉት ደግሞ የከተማዋ ነዋሪ ሐጂ ዝናቤ ኑርዬ ናቸው፡፡

በተለይም በከተማዋ ሰላምን ለማስፈን ወላጆች ልጆቻቸውን በመምከርና በማስተማር የሚጠበቅባቸውን ግዴታ መወጣት እንዳለባቸው አስገንዝበዋል፡፡

እሳቸውም ለከተማዋ ሰላም የራሳቸውን አስተዋጽኦ እያበረከቱ መሆናቸውን የገለጹት ሐጂ ዝናቤ በቀጣይም ይህንን ጥረት አጠናክረው ለማስቀጠል እንደሚሰሩ ተናግረዋል፡፡

ሌላው የውይይቱ ተሳታፊ ወጣት ኝግዎ ኡሞድ በሰጠው አስተያየት መንግስት ህዝቡ የሚያነሳቸውን የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች በወቅቱ ሊመልስ ይገባል፡፡

በተለይም ህዝቡ የሚያነሳቸውን የልማት ጥያቄ ቃል ከመግባት ባሻገር መንግስት ትኩረት ሰጥቶ መመለስ እንዳለበት ጠቁሞ ወጣቱም ከመንግስት ጎን በመሆን የተጀመረውን ለውጥ ለማስቀጠል በትኩረት ሊሰራ እንደሚገባ ጠቁሟል፡፡

ሌላው የውይይቱ ተሳታፊ አቶ ጆን ኡጁንግ በበኩላቸው የከተማዋን ሰላም የማስጠበቅ ሥራ በህዝቡ እጅ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በተለይም የከተማዋን ሰላም የማስጠበቁ ሥራ በእያንዳንዱ ቤተሰብ እጅ መሆኑን ጠቅሰው ሁሉም ለሰላም ዘብ ሊቆም እንደሚገባም ጠቁመዋል፡፡

በከተማዋ ከመልካም አስተዳደር በተለይም ከማዘጋጃ ቤት አገልግሎት አሰጣት ጋር ተያይዘው የሚነሱ ችግሮችን ለመፍታት መንግስት በትኩረት ሊሰራ እንደሚገባም ጠይቀዋል፡፡

የክልሉ ርዕሰ መስተዳደር አቶ ኡሞድ ኡጁሉ ለተነሱ ጥያቄዎች በሰጡት ምላሽ መንግስት በከተማዋ የሚነሱ የልማትና የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመፍታት ትኩረት አድርጎ እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በተለይም በከተማዋ የሚሰተዋሉ የአገልግሎት አሰጣጥ ችግሮችን ለመፍታት በየቀበሌ የሚገኙ የአመራር አካላትን በማጣራት መፍትሄ ለመስጠት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በቀጣይም ''የክልሉ መንግስት ከህብረተሰቡ የሚነሱ የልማትና የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመፍታት ይሰራል'' ብለዋል፡፡

ህብረተሰቡም የተጀመረውን ለውጥ እውን ለማድረግና የሚነሱ ችግሮችን ለመፍታት የሚደረገውን ጥረት ለመደገፍ ከመንግስት ጎን በመሆን ድጋፉን ማጠናከር እንዳለበት አሳስበዋል፡፡

በውይይቱ ላይ ከ300 በላይ የከተማዋ ነዋሪዎች ታድመውበታል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም