በዞኑ የተሽከርካሪ አደጋን ለመቀነስ በተደረገው ጥረት መሻሻል መምጣቱ ተገለጸ

63
አምቦ ግንቦት 17/2010 በምዕራብ ሸዋ ዞን የትራፊክ አደጋን ለመቀነስ በተደረገው ህብረተሰብ አቀፍ ጥረት መሻሻል መምጣቱ  ተገለጸ፡፡ የዞኑ ፖሊስ መምሪያ የትራፊክ ማኔጅመንት ዲቪዥን ኃላፊ ኮማንደር ተሰማ ብሩ ለኢዜአ እንዳሉት  ባለፉት ዘጠኝ ወራት  አምቦን ጨምሮ በዞኑ 48 የተሽከርካሪ  አደጋዎች ደርሰው  የ53 ሰዎች ህይወት አልፏል፡፡ ይህም ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር  በአደጋው ብዛት በ19 ፣ በሟቾች ቁጥር ደግሞ በ27  ቀንሷል ። የንብረት ጉዳትም በ10 ሚሊዮን ብር በመቀነስ መሻሻል አሳይቷል ። ባለፉት ዘጠኝ ወራት  ከ180 ሺህ በላይ ለሚሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎች በእግረኞች የመንገድ አጠቃቀም ፣በትራፊክ አደጋ አስከፊነትና ተያያዥ ጉዳዮዮች ዙሪያ የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርት መሰጠቱ ለአደጋው መቀነስ አስተዋጽኦ ማድረጉን ኮማንደር ተሰማ  ተናግረዋል፡፡ ለተሽከርካሪ አደጋ መንስኤ የሆነው የእግረኞች የመንገድ አጠቃቀም እየተሻሻለ በመምጣቱና እግረኞች የግራ መስመራቸውን ይዘው መጓዛቸው  ሌላው ምክንያት እንደሆኑም ተጠቅሷል፡፡ ኮማንደሩ እንዳመለከቱት ለ3ሺህ  376 አሽከርካሪዎችም በትራፊክ ህግ አጠቃቀም ዙሪያ ስልጠና ተሰጥቷል፤ ከፍጥነት በላይ በማሽከርከር፣ ትርፍ ሰው በመጫንና ሌሎችንም  የትራፊክ ደንቦችን ተላልፈው የተገኙ 8 ሺህ 178 አሽከርካሪዎች ከሶስት ሚሊዮን ብር በላይ እንዲቀጡ  ተደርጓል። አብዛኛውን ጊዜ የትራፊክ አደጋ የሚደርሰው በሀሰተኛ መንጃ ፈቃድ በሚያሽከረክሩ ግለሰቦች መሆኑን ያመለከቱት  ኮማንደሩ በዚህ ረገድም በተደረገ ጥብቅ ክትትል 41 አሽከርካሪዎች ተይዘው ጉዳያቸው በህግ እየታየ ነው፡፡ የዞኑን የትራፊክ እንቅስቃሴ ለማገዝም ለ216 ተማሪዎች በመሰረታዊ የትራፊክ ህግ ዙሪያ ስልጠና ተስጥቶ በተማሪዎች መግቢያ እና መውጫ ጊዜያት አገልግሎት እየሰጡ ይገኛሉ ተብሏል፡፡ የአምቦ ከተማ ነዋሪው አቶ ፍቃዱ ታደሰ በሰጡት አስተያየት በከተማው በትራፊክ ፖሊሶች መደረግ ስላለበት ጥንቃቄ እየተሰጠ ባለው የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርት  የእግረኞች የመንገድ አጠቃቀም መሻሻሉን ተናግረዋል፡፡ ከዚህ በፊት ሁሉም በዘፈቀደ መንገድ ያቋርጥ እንደነበር መታዘባቸውን አስታውሰው " እግረኞች ግራ መስመራችንን ብቻ ይዘን መጓዛችን ከትራፊክ አደጋ ስጋት ነጻ እንድንሆን ረድቶናል " ብለዋል፡፡ በአምቦ አዲስ ከተማ ትምህርት ቤት የአስረኛ  ክፍል ተማሪና ረዳት ትራፊክ የሆነው ወጣት ሄኖክ ዘለዓለም  በበኩሉ ያገኘውን ስልጠና ተጠቅሞ  በተማሪዎች መግቢያ እና መውጫ ጊዜ ለተማሪዎች የትራፊክ አገልግሎት እየሰጠ መሆኑን ተናግሯል፡፡ በተማሪዎች ላይም ከዚህ ቀደም መንገድ ሲያቋርጡ ይደርስ የነበረው አደጋ ረዳት ትራፊክ ተማሪዎቹ በሚሰጡት አገልግሎት መቀነሱን ጠቁሟል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም