የሊጉ ጉባኤ የማዕከላዊ ኮሚቴና የቁጥጥር ኮሚሽን አባላትን መረጠ

79

መቀሌ ታህሳስ 23/2011 በመቀሌ ከተማ ሲካሄድ የቆየው የህወሓት  ወጣት ሊግ ጉባኤ ለቀጣይ ሁለት ዓመታት የሚመሩ 30 የማዕከላዊ ኮሚቴና የቁጥጥር ኮሚሽን አባላትን በመምረጥ  ተጠናቀቀ፡፡

ጉባኤው ትናንት ማምሻውን ከመጠናቀቁ በፊት ከተመረጡ የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት መካከል ሊቀመንበርና ምክትል ሊቀመንበር እንዲሁም ዘጠኝ  ስራ አስፈፃሚዎች ተሰይመዋል።

ከሊጉ  ሊቀመንበርነት በክብር የተሰናበተው ወጣት ሰናይ ካህሰ እንዳለው፣የተመረጡ አዲስ አመራሮችም የውስጥ አደረጃጀታቸውን ሳያጠናክሩ የወጣቱ ጥያቄ መመለስ እንደማይችሉ አውቀው በብቃት ሊመሩ ይገባል።

ከጉባኤው ተሳታፊ ከነበሩት መካከል  ወጣት ኒቀዲሞስ ገብረኪዳን በሰጠው አስተያየት " አሁን ያለን ወጣቶች የትናንት የወላጆቻችን ታሪክ፣ ትጥቅና ስንቅ ተጠቅመን በጸረ ድህነት ትግል ላይ መዝመት ይጠበቅብናል" ብሏል።

ባለፉት ዓመታት የተመዘገቡ የልማትና የእድገት ውጤቶች ለማስጠበቅ ወጣቶች በትጋት መስራት እንዳለባቸው ያመለከተው ደግሞ አዲስ ከተመረጡት ማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት መካከል  ወጣት ሪሐና መሃመድ ናት፡፡ 

" ያሰብውን ልማትና ዴሞክራሲ ከዳር ማድረስ የሚቻለው ህግ መንግስታዊ ስርዓታችን ሲከበር መሆኑን አውቀን ዘብ ልንቆም ይገባል" ብላለች።

ሌላው የጉባኤው ተሳታፊ ወጣት መሃሪ ገብረሃና በበኩሉ ሰላም የሰፈነባትና ፈጣን ልማት የተረጋገጠባት ክልልና ሀገር ማረጋገጥ የሚቻለው ወጣቶች በግንባር ቀደምትነት ሲንቀሳቀሱ መሆኑን ተናግሯል፡፡

" ይህንን በተግባር ለመተርጎም ተዘጋጅተናል" ብሏል።

" የፅናትና የድል ጉባኤ " በሚል መሪ ሀሳብ በተካሄደው ጉባኤ ከ700 የሚበልጡ የሊጉ  አባላትና ጥሪ የተደረገላቸው  እንግዶች ተሳትፈዋል፡፡

ጉባኤው የተጠናቀቀው ባለ ዘጠኝ ነጥብ የአቋም መግለጫ በማውጣት ሲሆን  የህወሓት ወጣት ሊግ  ከ315 ሺህ  በላይ አባላት እንዳሉትም ተመልክቷል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም