ሲስተም የለም በሚል ምክንያት የመብራት አገልግሎት ልናገኝ አልቻልንም -- ተጠቃሚዎች

71

ታህሳስ 23/2011 ሲስተም የለም በሚል ምክንያት ካለፈው ሳምንት ጀምሮ የመብራት አገልግሎት ማግኘት አለመቻላቸውን የአዲስ አባባና አካባቢዋ አንዳንድ የካርድ ክፍያ ተጠቃሚዎች ተናገሩ፡፡

በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የደቡብ አዲስ አበባ ሪጅን ካዛንቺስ ቅርንጫፍ ካገኘናቸው ነዋሪዎች መካከል ከቱሉ ዲምቱ እንደመጡ የሚናገሩት ወይዘሮ መስከረም ዲንሳሰ “ካርድ የምንሞላው አቃቂ ቢሆንም ባለፈው ሀሙስ አቃቂ ሲስተም የለም ተብዬ ወደ ተለያዩ ቦታዎች ቢሄድም አገልግሎቱን ላገኝ አልቻልኩም” ነው ያሉት፡፡

በአቃቂ ቃሊቲ ቅርንጫፍ ከሶስት ቀን መጉላላት በኋላ ከሌሊቱ 11 ሰዓት ተኩል አካባቢ ካዛንቺስ ብገኙም እስካሁን የአገልግሎቱ ተጠቃሚ ልሆኑ አለመቻላቸውን ነው የገለጹት።  

ከአዲሱ ገበያ አካባቢ እንደመጡ የሚናገሩት ሌላው ተገልጋይ አቶ አበበ ደምስ በበኩላቸው ቤት ውስጥ ህጻናት በጭለማ አስቀምጠው በከተማዋ የካርድ ክፍያ ጣቢያዎች አሉ የተባሉበት በሙሉ ብያዳርሱም አገልግሎቱን ማግኘት እንዳልቻሉ ነው የተናገሩት።  

ከሱሉልታ የመጣው ወጣት ፍቃዱ ተፈራ እንደተናገረው የአንድ መቶ ብር ካርድ ለመሙላት ከስልሳ ብር በላይ የትራንስፖርት ወጪ ማውጣቱን ተናግሮ፤ በሲስተም ለማስሞላት በየአካባቢው መቋቋም ሲገባው አሁን ደግሞ አገልግሎቱ የሚሰጥበት አካባቢም ሲስተም የለም እየተባለ ለችግር መዳረግ የለብንም ብሏል።  

 “ቴክኖሎጂው ከሰው አቅም በላይ ሊሆን አይችልም፤ የአሰራር ችግር ነው” ሲል  የተናገረው ወጣቱ በተለይ በአካባቢው እንጀራ እየጋገሩ የሚሸጡ እናቶች ገቢያቸው ከመቅረቱም በላይ ካርድ ለማስሞላት በሚያደርጉት እንቅስቃሴ በኑሯቸው ላይ ጫና እንዳሳደረ መመልከቱንም ጠቁሟል፡፡

ከቃሊቲ አካባቢ እንደመጡ የሚናገሩት ሌላው የአገልግሎቱ ተጠቃሚ  አቶ እሼቱ መሀመድ ከባለፈው አርብ ጀምሮ በአካባቢያቸው የሚገኘው ጣቢያ ሲስተም ተበላሽቷል በሚል አገልግሎቱ በመቋረጡ ዛሬ ሌሊት አስር ሰዓት መጥተው የመጀመሪያ ተሰላፊ ቢሆኑም ዘገባው እስከተሰራ ድረስ አገልግሎት ማግኘት ባለመቻላቸው  ቅሬታቸውን ገልፀዋል።

“አዲስ አበባን ስናካልል ቆይተን እዚህ ካዛንቺስ ተገኝቻለሁ” ያሉት ከለገጣፎ እንደመጡ የሚናገሩት ሼህ በድሩ ናስር በችግሩ ምክንያት ስራችንን በአግባቡ ልንሰራ አልቻልንም ብለዋል፡፡

ከካራ ቆሬ እንደመጡ የሚናገሩት አቶ ተስፋ ካላይ በበኩላቸው የሲስተም መቋረጥ ብቻ ሳይሆን የአሰራር ችግር መሆኑን ተናግረው በተለይ በዓል ሲመጣ መብራት ሀይል አሰራሩን ሊያስተካከል ይገባል ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥቷል፡፡

በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የአውቶሜሽንና ኢነርጂ ማኔጅመንት ምክትል ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ደመቀ ሮቤ ስለ ሁኔታው ተጠይቀው በቅድመ ክፍያ ካርድ አገልግሎት ላይ ችግሩ የተፈጠረው ካለፈው ዓርብ ጀምሮ መሆኑን ተናግረዋል።

የአገልግሎቱ መቋረጥ መንስኤ መጀመሪያ የኔት ወርክ ችግር እንደነበርና ከኢትዮ ቴሌኮም ጋር በመነጋገር የተፈታ ቢሆንም በድጋሚ በመስሪያ ቤታቸው በሚገኘው ሰርቨር ዳታ ላይ በደረሰ ብልሽት ችግሩ ተባብሶ ሊቀጥል መቻሉንም ገልጸዋል።

በአሁኑ ወቅት የድርጅቱን ባለሙያዎችና ሌሎች አጋዥ አካላትን በማሰማራት ሲስተሙን ስራ ለማስጀመር ጥረት እየተደረገ እንደሚገኝ የተናገሩት አቶ ደመቀ ከነገ ጀምሮ በሁሉም ጣቢያዎች አገልግሎቱን ለመስጠት  እየተሰራ መሆኑንም  ተናግረዋል።

የህብረተሰቡን ችግር በመረዳት አገልግሎቱን ከስራ ሰዓት ውጭ ጭምር በመስጠት ለመፍታትም እንቅስቃሴ እየተደረገ ነው ሲሉ አቶ ደመቀ ጨምረው ገልፀዋል፡፡  

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም