በሶዶ ከተማ በእሳት ቃጠሎ ንብረት የወደመባቸውን የማቋቋም ስራ ተጀመረ

72

ሶዶ ታህሳስ 23/2011 በወላይታ ሶዶ ከተማ ከትላንት በስቲያ ተከስቶ በነበረው የእሳት አደጋ ንብረት የወደመባቸውን ነዋሪዎች የማቋቋም ስራ መጀመሩን የከተማው አስተዳደር አስታወቀ።

በአደጋው ከ13 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት ንብረት መውደሙ ተገልጿል።

የከተማው ፖሊስ አዛዥ ዋና ኢንስፔክተር ያልሳ ጋጋ እንደገለፁት ከትላንት በስቲያ ከሌሊቱ 11፡30 አካባቢ በመርካቶ ክፍለ ከተማ በተለምዶ ማሪያም ሰፈር ተብሎ በሚጠራ አካባቢ በደረሰው የእሳት አደጋ ጉዳት የደረሰባቸው ነዋሪዎችን ለማቋቋም ዘጠኝ አባላት ያሉት ኮሚቴ ተቋቁሟል ።

ነዋሪዎችን በማሳተፍ የተቋቋመው ኮሚቴ ከከተማ አስተዳደሩ ማህበራዊ ዋስትና እና ንግድና ኢንዱስትሪ ተቋማት ጋር በቅንጅት የሚሰራ መሆኑን ተናግረዋል ።

በቃጠሎው የንብረት ውድመት የደረሰባቸው ነዋሪዎች ዘጠኝ መሆናቸውን የገለጹት ዋና ኢንስፔክተሩ የወደመው ንብረት 13 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር እንደሚገመት መረጋገጡን ተናግረዋል ።

እንደ ኢኒስፔክተሩ ገለጻ በፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን የፎረንሲክ ምርመራ ቡድን አማካኝነት የአደጋው ክስተት መንስኤ እየተጣራ ነው፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም