በካማሽ ዞን ትምህርት ያቋረጡ 37 ሺህ ተማሪዎች ወደ ትምህርት ለመመለስ እየተሰራ ነው

53

ሶሳ ታህሳስ 22/2011 በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በካማሽ ዞን ግጭት ከትምህርት ገበታ ውጪ የሆኑ 37 ሺህ ተማሪዎችን ወደ ትምህርት ለመመለስ እየተሰራ መሆኑን የክልሉ ትምህርት ቢሮ ገለጸ፡፡

በክልሉ በትምህርት ቤቶች ሰላማዊ የመማር ማስተማር ሂደትን የሚያጠናክር ውይይት በአሶሳ ተጀምሯል፡፡

የክልሉ ትምህርት ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ በሽር አብዱራህማን እንዳስታወቁት በዞኑ በጸጥታ ችግር የተዘጉትን 82 አንደኛና 15 ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶችን ሥራ ለማስጀመር ጥረት እየተደረገ ነው።

ትምህርት ቤቶቹ  በአካባቢው በተፈጠረው ችግር የዓመቱን ትምህርት ሳይጀምሩ የቆዩ ናቸው፡፡

በግጭቱ አራት ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ሙሉ በሙሉ ሲወድሙ 10 የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ደግሞ በከፊል ጉዳት እንደደረሰባቸው አስረድተዋል፡፡

በትምህርት ቤቶቹ ከ36ሺህ በላይ ተማሪዎች  ትምህርታቸውን ማቋረጣቸውን ገልጸዋል፡፡

ትምህርቱን እንደገና ለማስጀመር የትምህርት ተቋማትን ሰላምን የሚያጠናክሩ ጉዳዮች ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት እየተደረገ ነው፡፡

መድረኩ በአሶሳና መተከል ዞኖች እየተካሄደ እንደሚገኝ ጠቅሰው፣ የሃይማኖት አባቶች፣ የአገር ሽማግሌዎችና ሌሎችም እንደተሳተፉበት ገልጸዋል፡፡

በዞኑ ትምህርቱን ለማስቀጠል በቅርቡ የአካባቢውን ሠላም ወደ ነበረበት ለመመለስ ከተቋቋመው ኮማንድ ፖስት እንቅስቃሴ በመከተል የሚከናወኑ ተግባራት እንዳሉም አብራርተዋል፡፡

በተለይም የወደሙ ትምህርት ቤቶችን በጊዜያዊ መጠለያ በመተካት በረጅም ጊዜ መልሶ ለመገንባትና ቁሳቁስ አሟልቶ ሥራ ለማስጀመር ኅብረተሰቡን፣ ግብረ-ስናይ ድርጅቶችን በማሳተፍ ጥረቱ መቀጠሉን አመልክተዋል፡፡

“በካማሽ ዞን ወደሚገኙ አምስት ወረዳዎች የሚያስገቡ መንገዶች በቅርቡ ሙሉ በሙሉ እንደሚከፈቱ ተስፋ ተደርጓል” የሚሉት አቶ በሽር፣ በተለይም የባከነውን የትምህርት ጊዜ ለማካካስ ከወላጅ መምህራን ኅብረት ጋር ምክክክር እንደሚደረግ ጠቅሰዋል፡፡

ግጭቱን ሸሽተው ከዞኑ የወጡ መምህራን ደመወዛቸውን እንዲያገኙ እየተደረገ መሆኑንም  አመልክተዋል፡፡

ለሁለት ቀናት በሚቆየው በዚሁ የውይይት መድረክ ከ150 የሚበልጡ ባለድርሻ አካላት እየተሳተፉ ነው፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም