ዐቃቤ ህግ በሜጀር ጄኔራል ክንፈ ዳኘው ላይ የጠየቀው የ10 ቀን የክስ መመስረቻ ጊዜ ተፈቀደ

68

አዲስ አበባ ታህሳስ 22/2011 የፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት በሜጀር ጄኔራል ክንፈ ዳኘው ላይ ዐቃቤ ሕግ የጠየቀውን የ10 ቀን የክስ መመስረቻ ጊዜ ፈቀደ።

የቀድሞው የብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን /ሜቴክ /ዋና ዳይሬክተር ሜጀር ጄኔራል ክንፈ ዳኘው ዛሬ የፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት 10ኛ ወንጀል ችሎት ቀርበዋል።

መርማሪ ፖሊስ ሜጀር ጄኔራል ክንፈ ከተጠረጠሩበት የ19 የሙስና መዝገቦች ውስጥ ሶስቱን በማጠናቀቅ ዛሬ ለፌዴራል ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ ማስረከቡን ለፍርድ ቤቱ ገልጿል።

የተጠናቀቁት መዝገቦች የመርከብ ጥገናና ግዢ፣ የሪቬራ ፕላስቲክ ፋብሪካ ሽያጭና ከኢምፔሪያል ሆቴል ግዢ ጋር የተያያዙት መሆናቸውን  ፖሊስ ለፍርድ ቤቱ ገልጿል።

''ፖሊስ ምርመራውን ሙሉ በሙሉ አጠናቆ ሳይጨርስ ለዐቃቤ ህግ የተወሰኑ መዝገቦችን ማስረከቡ አግባብነት የለውም፤ በውስጠ ተዋቂነትም ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ የሚጠይቁ ያስመስላል'' ሲሉ የሜጀር ጄኔራል ክንፈ ዳኘው ተከላካይ ጠበቆች ተከራክረዋል።

በመሆኑም ተጠርጣሪው  ሜጀር ጄኔራል ክንፈ የዋስትና መብታቸው ተከብሮ ጉዳያቸውን በውጪ ሆነው እንዲከታተሉም ጠበቆቻቸው ፍርድ ቤቱን ጠይቀዋል።

ተጠርጣሪው ሜጀር ጄኔራል ክንፈ ዳኘው የተጠረጠሩበት ከባድ የሙስና ወንጀል በመሆኑ ተከላከይ ጠበቆች ያቀረቡትን የዋስትና  ጥያቄ ፍርድ ቤቱ ውድቅ አድርጓል።

ፖሊስ ሜጀር ጄኔራል ክንፈ በሙስና የተጠረጠሩባቸውን ሌሎች 16 መዝገቦች ተያያዥነት ያለቸው በመሆኑ ጎን ለጎን በቀሪዎቹ ላይ  የምርመራ ስራውን እንደሚያጠናቅቅ ነው የገለጸው።

የግራ ቀኙን ክርክር ያደመጠው ፍርድ ቤቱ ዐቃቤ ህግ የክስ መመስረቻ ቀን እስከ 15 ቀናት ድረስ መጠየቅ የሚያስችለው የሕግ አግባብ ያለ በመሆኑ የተጠየቀው ጊዜ የተጠርጣሪውን መብት የሚያስከብር ነው ብሏል።

በዚህ መሰረትም አቃቤ ሕግ የጠየቀውን የ10 የክስ መመስረቻ ቀን በመፍቀድ ለጥር 2 ቀን 2011 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም