ኢትዮጵያና ሱዳን የመንግስታት ብቻ ሳይሆን የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት አላቸው-ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ

97

አዲስ አበባ ታህሳስ 23/2011 የኢትዮጵያና ሱዳን ግንኙነት የመንግስታት ብቻ ሳይሆን የህዝብ ለህዝብ መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ ተናገሩ። 

ዶክተር ወርቅነህ ለይፋዊ የስራ ጉብኝት ትናንት ወደ ካርቱም ያቀኑ ሲሆን በዚህም ከጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የተላከውን መልዕክት ለሱዳኑ ፕሬዚዳንት ኦማር ሐሰን አልበሽር አድርሰዋል።

መልዕክቱም ሁለቱ አጋራት በአህጉራዊና ቀጠናዊ ጉዳዮች ላይ በጋራ ለመስራት የሚያስችላቸው መልዕክት መሆኑ ተገልጿል።

ዶክተር ወርቅነህ ከሱዳኑ ፕሬዝዳንት ኦማር ሐሰን አልበሽር ጋር በሁለትዮሽና ክልላዊ ጉዳዮች ዙሪያ ውይይት ማድረጋቸውንም የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽህፈት ቤት ለኢዜአ በላከው መግለጫ አስታውቋል።

ሚኒስትሩ እንዳሉት በቅርቡ ከአንድ ሺህ በላይ ኢትዮጵያዊያን ከሱዳን የተለያዩ እስር ቤቶች በነፃ መለቀቃቸው የሁለቱን አገራት ህዝቦች ግንኙነት መጠናከር እንደሚያሳይ ገልጸዋል።

ፕሬዚዳንት አልበሽር በበኩላቸው የሁለቱ አገር ህዝቦች በመከራም ሆነ በደስታ ጊዜ ለዘመናት አብረው የኖሩና ወደፊትም አብረው የሚቀጥሉ   ወንድምና እህት ህዝቦች መሆናቸውንም በውይይታቸው ገልፀዋል።

ፕሬዝዳንት አልበሽር በንግግራቸው ''በሱዳን የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን በአገራቸው የሚኖሩ ያህል እንዲሰማቸው እንደሚሰሩም'' ጠቁመዋል።

በማያያዝም ''የኢትዮጵያ ሰላምና ደህንነት ከሱዳን የአገራዊ ደህንነት ጉዳይ ጋር የተያየዘ ነው'' ሲሉም ተናግረዋል።

በተጨማሪም የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ከሱዳኑ አቻቸው ኤል-ዳልዲሪ መሐመድ አህመድ ጋር በሁለትዮሽ ጉዳዮች ላይ ተወያይተዋል።

ሚኒስትሩ ኤል-ዳልዲሪ መሐመድ አህመድ በዚሁ ወቅት እንዳሉት ከኢትዮጵያ ጋር በአህጉራዊና ቀጠናዊ ጉዳዮች በጋራ ለመስራትና በተለይም በደቡብ ሱዳንና በሶማሊያ ያለውን ሁኔታ በተመለከተ ውይይት አካሄደዋል።

ኤል-ዳልዲሪ መሐመድ አክለውም ዶክተር ወርቅነህ ከጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ይዘውት የመጡት መልዕክት  በሁለቱ አገራት ግንኙነትን ለማጠናከር የሚያስችል መልእክት መሆኑን አስረድተዋል።

ሁለቱ አገሮች በአፍሪካ አህጉር ደረጃና በአፍሪካ ቀንድ ኢኮኖሚያዊ ውህደትን ለማምጣት በሚደረገው ጥረት  እንዲሁም የአህጉራዊ ሰላምና መረጋጋትን ለማስፋፋት በአንድነት ተባብረው ለመስራት መስማማታቸው ይታወቃል።

ፕሬዚዳንት ኦማር ሐሰን አልበሽር በያዝነው ወር መጀመሪያ በኢትዮጵያ ይፋዊ የስራ ጉብኝት ማድረጋቸው ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም