በጎንደር ከተማ ሀሰተኛ ወሬ አሰራጭተዋል የተባሉ አራት ግለሰቦች በገንዘብ ተቀጡ

65

ጎንደር ታህሳስ 22/2011 በጎንደር ከተማ ሀሰተኛ ወሬ በማሰራጨት በህዝቡ ዘንድ ድንጋጤ እንዲጠፈር አድርገዋል የተባሉ አራት ግለሰቦች በገንዘብ መቀጣታቸውን የከተማ አስተዳደሩ ፍትህ መምሪያ አስታወቀ።

የመምሪያው ሃላፊ አቶ ግርማ ጌታቸው ለኢዜአ እንደተናገሩት ግለሰቦቹ ቅጣቱ የተላለፈባቸው ህጻናትን ወደ ትምህርት ቤት በባጃጅ ለማድረስ የወሰዳቸው የባጃጅ ሾፌር ትምህርት ቤት ሳያደርስ ጉዳት አድርሶባቸዋል በማለት ያልተረጋገጠ ወሬ በማሰራጨታቸው ነው፡፡

ፖሊስና ዐቃቢ ህግ ጉዳዩን ለማጣራት ባደረጉት ምርመራም በከተማው ታህሳስ 9 ቀን 2011ዓ.ም ተፈጸመ የተባለው ድርጊት በከተማው ፖሊስ ጣቢያዎች የተመዘገበ የወንጀል ድርጊት አለመኖሩ ማረጋገጥ ችለዋል፡፡

ግለሰቦቹ ያሰራጩት የፈጠራ ወሬ መሆኑን ፖሊስ ግለሰቦቹን በቁጥጥር ስር በማዋል ያደረገውን ምርመራ በማጠናቀቅ አቃቤ ህግ ክስ እንዲመሰረትባቸው አድርጓል፡፡

የመጀመሪያ ተከሳሽ ወይዘሮ በላይነሽ አዳነ የሀሰተኛ ወሬ ጠንሳሽ ሲሆኑ ወይዘሮ አትክልት ፈለቀና ሃምሳ አለቃ እንይሽ ቸኮል ደግሞ የወይዘሮ በላይነሽ አዳነን የሀሰት ወሬ በማመን ወሬው እንዲዛመት ያደረጉ ናቸው፡፡

መምህር ይትባረክ ሀይለእየሱስ የተባሉ የቤተ-ክርስቲያን አገልጋይ ደግሞ ጥንቃቄ ሳያደርጉና እውነታውን ሳያረጋግጡ ቤተ-ክርስቲያን ለተሰበሰበ ህዝብ የሀሰት ወሬው እንደተፈጸመ አድርገው መልእክቱ እንዲተላለፍ አድርገዋል፡፡

እድሜአቸው ከ22 እስከ 59 አመት የሚደርሰው እነዚሁ ተከሳሾች እውነታውን ሳያረጋግጡ ሀሰተኛ ወሬ ማውራታቸው ፖሊስ በሰውና በሰነድ ማስረጃ ያረጋገጠባቸው ናቸው፡፡

በ1996ዓ.ም ተደንግጎ የወጣውን የኢፌድሪ የወንጀል ህግ አንቀጽ 32/1/ሀ እና 485/1 የተመለከተውን በመተላለፍ አቃቢ ህግ በመሰረተባቸው ክስ ግለሰቦቹ በፍርድ ቤት ድርጊቱን መፈጸማቸውን አምነዋል፡፡

የጎንደር ከተማ አስተዳደር ፍርድ ቤትም ባለፈው አርብ በዋለው ችሎት ግለሰቦቹ የቤተሰብ አስተዳዳሪ መሆናቸውንና ከዚህ ቀደም የፈጸሙት የወንጀል ድርጊት አለመኖሩን በቅጣት ማቅለያነት በመቀበል እያንዳንዳቸው የአንድ ሺ ብር የገንዘብ መቀጮ እንዲከፍሉ ብይን ሰጥቷል፡፡

አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ የከተማው ነዋሪዎች በበኩላቸው በከተማው የተሰራጨው ሀሰተኛ ወሬ በተለይ ወላጆች ልጆቻቸውን ወደ ትምህርት ቤት ለመላክ ስጋት ፈጥሮ እንደነበር አስታውሰዋል፡፡

ወይዘሮ መልሺው ንጉሴ የተባሉ ነዋሪ ''ወሬውን ስሰማ ከፍተኛ ድንጋጤ ፈጥሮብኝ ልጄ ወደ ትምህር ቤት እንዳትሄድ አድርጌ ነበር'' ብለዋል፡፡

ጥፋተኛ በተባሉት ግለሰቦች ላይም ፍርድ ቤት ያስተላላፈው ብይን አስተማሪነት አለው ሲሉ ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም