የስራ እድል ፈጠራ ለተጀመረው የለውጥ ጉዞ ህልውና ነው -አቶ ካሳሁን ጎፌ

120

አዲስ አበባ ታህሳስ 22/2011 የስራ እድል ፈጠራ ለተጀመረው የለውጥ ጉዞ ህልውና መሆኑን መገንዘብ ይገባል ሲሉ የከተማ ልማት ኮንስትራክሽን ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ካሳሁን ጎፌ ገለጹ።

ከመላ ሀገሪቷ የተውጣጡ ሞዴል ኢንተርፕይዞች ምርቶቻቸውን ለህዝብ የሚያቀርቡበትና ከህብረተሰቡ ጋር የገበያ ትስስር የሚፈጥሩበት ሀገር አቀፍ ኤግዚብሽንና ባዛር በዛሬው እለት በአዲስ አበባ ከተማ ክፍት ሆኗል።

ኤግዚብሽንና ባዛሩን የከፈቱት የከተማ ልማት ኮንስትራክሽን ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ካሳሁን ጎፌ "የአያት ቅድመ አያቶቻችንን እውቀትና ጥበብ የሚያሳዩ የታሪክ አሻራ ባለቤት የነበረችው ኢትዮጵያን በድጋሚ ስሟን ከፍ ለማድረግ ድህነት ላይ መዝመት ያስፈልጋል" ብለዋል።

ከድህነት ለመውጣት፣የተጀመረውን የለውጥ ጉዞ  ለማስቀጥልና ዜጎችን ተጠቃሚ ለማድረግ ደግሞ ይህ ዘርፍ ድርሻው ትልቅ ነው ብለዋል።

የጥቃቅንና አንስተኛ ኢንተርፕራይዝ ልማት ከትንሽ ነገር ተነስቶ በሂደት ወደ ባለሀብትነት የሚለወጡበት ዘርፍ በመሆኑም ከድህነት ከምንወጣባቸው መንገዶች አንዱና ቁልፉ ተግባር ነው ብለዋል።

በመሆኑም በዚህ ዘርፍ የተሰማሩ ስዎች በሚጠበቀው ልክ ለውጡን የሚያፋጥኑ እንዲሆኑና የተጀመረውን ለውጥ ለማስቀጠል ህብረተሰቡ መደገፍና ማበረታት ይገባዋል ሲሉም አሳስበዋል።

በኢግዚብሽንና ባዛሩ ምርቶቻቸውን ለህብረተሰቡ ያቀረቡ ኢንትርፕራይዞች በበኩላቸው የመስሪያ ቦታ ና የመሸጫ ቦታ ችግር በሚፈልጉት ደረጃ ለማደግ እንቅፋት መፍጠሩን  ገለጸዋል።

እንዲሁም ምርቶቻቸውን ከሀገር ውስጥ ባለፈ ወደ ውጭ ለመላክ  አመቺ ሁኔታ እንዲፈጠርላቸውም ጠይቀዋል።

በዚህ ኤግዚብሽንና ባዛር በጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራዝ በመደራጀት የተለያዩ ዘመናዊና ባህላዊ አልባሳት ፣የቆዳ ምርቶች፣የእደ ጥበብና ቅርጻ ቅርጽ ስራዎች፣ የብረታ ብረትና የእንጨት ስራዎች እንዲሁም ሌሎች የቴክኖሊጂ ስራ ምርቶች የሚቀርቡበት ነው።

ይህ ኤግዚብሽንና ባዛር ሜክስኮ በሚገኘው ዋቤ ሸበሌ ሆቴል ጎን በሚገኝ ክፍት ቦታ ላይ ከዛሬ ጀምሮ ለሰባት ተከታታይ ቀናት  ክፍት ሆኖ ይቆያል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም