ሚኒስቴሩ ባለፉት አምስት ወራት 83 ቢሊዮን ብር ገቢ ሰብስቧል

73

አዲስ አበባ ታህሳስ 22/2011 የገቢዎች ሚኒስቴር ባለፉት አምስት ወራት 83 ቢሊዮን ብር ገቢ መሰብሰቡን ገለጸ።

ሚኒስቴሩ በስሩ ያሉ ተጠሪ ተቋማትን ጨምሮ የ100 ቀን እቅድ አፈጻጸሙን በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለገቢዎች በጀትና ፋይናንስ ቋሚ ኮሚቴ ዛሬ አቅርቧል።

ተቋሙ በአምስት ወራት ውስጥ ከ102 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ ለመሰብሰብ አቅዶ ከአጠቃላይ ገቢ 83 ቢሊዮን ብር ሰብስቧል።

ይህ አፈፃፀም ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ከተሰበሰበው 76 ነጥብ 93 ቢሊዮን ብር ጋር ሲነፃፀር በ6 ነጥብ 07 ቢሊዮን ብር ጭማሪ አለው ተብሏል።

ከዚህ ውስጥ በመቶ ቀናት ለመሰብሰብ ከታቀደው ከ47 ቢሊዮን በላይ ብር በ80 ቀናት ውስጥ ከ38 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ መሰብሰቡን ሪፖርቱ ያሳያል።

ከዚህ ውስጥ በአምስት ወራት ውስጥ የተሰበሰበው የአገር ውስጥ ገቢ ከባለፈው ዓመት በ9 ቢሊዮን ብር ብልጫ አለው።

በሌላ በኩል ከአዳዲስ አልባሳት፣ ኤልክትሮኒክስና አደንዛዥ እጾች ከ406 ሚሊዮን ብር በላይ ግምት ያላቸው የኮንትሮባንድ ዕቃዎች መያዙንም ለምክር ቤቱ አቅርቧል።

የቋሚ ኮሚቴ አባላቱ ተቋሙ የገቢ አሰባሰብን ለማጠናከር የጀመረውን የለውጥ ስራ በጥንካሬ በማንሳት ማብራሪያ የሚፈልጉ ጉዳዮች ላይ ጥያቄ አንስተዋል።

በግብር ከፋዩ የሚነሱ ቅሬታዎችን በወቅቱ መፍታት፣ ህገ ወጥ የጦር መሳሪያና የገንዘብ ዝውውርን ለመከላከል በትብብር የተሰሩ ስራዎች፣ ከቀረጥ ነጻ የገቡ እቃዎች ባመጡት ለውጥ ላይ የተደረገ ጥናት ካለና ሌሎች ጥያቄዎችንም አንስተዋል።

የጉምሩክ ኮሚሽን ኮሚሽነር ደበሌ ቀበታ በሰጡት ማብራሪያ ህገ ወጥ የገንዘብ ዝውውርን ለመከላከል ስራዎች በትብብር  እየተሰሩ ቢሆንም አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱን አስረድተዋል።

ኢትዮጵያ የውጭ ምንዛሬ እጥረት አጋጥሟታል እየተባለ በርካታ ቁጥር ያለው የውጭ አገር ገንዘብ በየቀኑ መያዙ ምንጩ ከየት እንደሆነ ባንኮችን መፈተሽ እንደሚያስፈልግም ለምክር ቤቱ ጠቁመዋል።

ህገ ወጥ የጦር መሳሪያ በተለይም በሰሜን ምዕራብ ኢትዮጵያ እየጨመረ መምጣቱንና ህገ ወጥ የነዳጅ ዝውውርም በተመሳሳይ በመጨመሩ ከህገ ወጥነት ያለፈ በመሆኑ ልዩ ትኩረት እንዲሰጠው ለቋሚ ኮሚቴው አሳውቀዋል።

የገቢዎች ሚኒስትር ወይዘሮ አዳነች አቤቤ በበኩላቸው የሚሰበሰበው ገቢ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያሽቆለቆለ በመምጣቱ አገርን መምራት አስቸጋሪ የሆነበት ጊዜ ተደርሶ ነበር ብለዋል።

በመሆኑም ቀደም ሲል ተለይተው ሳይፈቱ የነበሩ ችግሮችን አመራሩ እንዲተገብር በማድረግ ባለፉት ሶስት ወራት የማነቃቃት ስራዎች ተሰርተዋል።

ከቀረጥ ነጻ አሰራርን በተመለከተ በአሰራሩ ኢትዮጵያ ማግኘት ያለባት ገንዘብ ወደ ግለሰቦች ኪስ መግባቱን አስረድተው ከ2002 እስከ 2010 ዓ.ም ከቀረጥ ነጻ ምክንያት ከ400 ቢሊዮን በላይ ብር ገቢ አለመሰብሰቡን አብራርተዋል።

ግብር በመክፈል የሚኮራ ህብረተሰብ ለመፍጠር ግንዛቤ የማስፋት፣ ኮንትሮባንድን ለመከላከል ጉምሩክ ፖሊስ የተሰኘ ቡድን የማቋቋምና ለሙስና አጋላጭ የሆኑ አሰራሮችን የማሻሻል ስራዎች መጀመራጀውንም አስረድተዋል።

የገቢዎች በጀትና ፋይናንስ ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ወይዘሮ ለምለም ሐድጉ በገቢ አሰባሰብ ከችግር ለመውጣት እየተወሰዱ ያሉ እርምጃዎችን  በጥንካሬ አንስተዋል።

ሚኒስቴሩ ህገ ወጥነትን ለመከላከል የፍተሻ ኬላዎችን ጨምሮ አጠቃለይ አሰራሩን በቴክኖሎጂ መደገፍ እንደሚገባ በመግለጽ በ5 ወራት ለመሰብሰብ ከታቀደው ቀሪውን ለማሳካት በትኩረት እንዲሰራም አሳስበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም