ማዕከሉ በጥቁር አፈር መሬት የሰብል አመራረት ዘዴ ለመቀየር የሚያስችል ቴክኖሎጂ እያስተዋወቀ ነው

102

ጎንደር ታህሳስ 22/2011 የጎንደር ግብርና ምርምር ማዕከል አርሶ አደሩ በዝናብ ውሃ በመታገዝ በጥቁር አፈር መሬት በአመት አንድ ጊዜ አንድ ሰብል የሚያመርቱበትን  አሰራር ለመቀየር የሚያስችል ቴክኖሎጂ እያስተዋወቀ መሆኑን ገለጸ፡፡

ቴክኖሎጂውን በሙከራ ደረጃ የተጠቀሙ አርሶ አደሮች  አዲሱ የግብርና አሰራር  ምርታቸውን በእጥፍ ማሳደግ እንዳስቻላቸው ተናግረዋል፡፡

ማዕከሉ ቴክኖሎጂውን በጣቁሳ ወረዳ መኮንታ ቀበሌ ትናንት ባዘጋጀው የገበሬዎች የመስክ በዓል ላይ አስተዋውቋል፡፡

የጎንደር ግብርና ምርምር ማዕከል ተመራማሪ የሆኑት አቶ ዘይኑ ጣሂር ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንደገለጹት ማዕከሉ ላለፉት ሁለት አመታት በ44 አርሶ አደሮች ሙከራ አድርጓል፡፡

 በ10 ነጥብ አምስት ሄክታር የጥቁር አፈር መሬት ማሳ ላይ ባካሄደው ምርምር በአመት ሁለት ጊዜ ማምረት የሚያስችል አጥጋቢ ውጤት ተገኝቷል፡፡

ስንዴና ሽንብራን በተከታታይ በማምረት ስንዴን በሄክታር 35 ኩንታል ሽንብራን ደግሞ 25 ኩንታል በአንድ የምርት ወቅት አርሶ አደሩ ማምረት እንደሚችል በሙከራው ማረጋገጥ መቻሉን ተመራማሪው አመልክተዋል፡፡

ከዚህ ቀደም አርሶ አደሩ ሰኔ፣ ሐምሌና ነሀሴ ወራትን የእርሻ መሬቱን ጦም በማሳደር መስከረም ላይ ሽንብራ ይዘራ እንደነበር ተመራማሪው ጠቁመዋል፡፡

ማዕከሉ ባቀረባቸው ’’ድንቅነሽ’’ የተባለች የስንዴና ’’ናቶሊ’’ የተባለ የሽንብራ ዝርያ አማካኝነት በአንድ የምርት ወቅት ሁለቱን በተከታታይ በማልማት ሁለት ጊዜ ማምረት መቻሉን ተመራማሪው ተናግረዋል፡፡

በጣቁሳ ወረዳ የመኮንታ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር አባይ ምስክር ከዚህ ቀደም በጥቁር አፈር መሬት ከአንድ ጊዜ በላይ ሰብል አምርተው እንደማያውቁ ተናግረዋል፡፡

የምርምር ማዕከሉ ባደረገላቸው የሙያ ድጋፍና ባቀረበላቸው ምርጥ ዘርና አዳዲስ የቴክኖሎጂ አሰራር በመታገዝ ስንዴና ሽንብራን በማልማት በአመት ሁለት ጊዜ ማምረት እንደቻሉ ገልጸዋል፡፡

ዘንድሮ ካለሙት ሩብ ሄክታር መሬት ስንዴ ስድሰት ኩንታል፣ ሽንብራ ደግሞ አምስት  ኩንታል እንደሚያገኙ ተናግረዋል፡፡

በጥቁር አፈር የእርሻ መሬት ከአንድ ጊዜ በላይ ሰብል አምርተው እንደማያውቁ የተናገሩት  በወረዳው የግባዛ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ሲሳይ ታከለ ናቸው፡፡

ምርምር ማዕከሉ ያቀረባቸው የስንዴና የሽንብራ ዝርያዎች ፈጥነው በመድረስና በምርታማነታቸው ጭምር የተሻሉ በመሆናቸው ቴክኖሎጂውን ተቀብለው ለመተግበር ፍላጎት እንዳደረባቸው ገልጸዋል፡፡

የጎንደር ግብርና ምርምር ማዕከል ኃላፊ አቶ አስፋው አዛናው የግብርና ቴክኖሎጂው የአርሶ አደሩን ምርታማነት የሚጨምር በመሆኑ የግብርና ባለሙያዎች ቴክኖሎጂውን በማስፋት ረገድ አርሶ አደሩን ሊደግፉ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

የአማራ ክልል ግብርና ምርምር ኢንሲቲትዩት የሰብል ዳይሬክተር ዶክተር አለማየሁ አሰፋ አዳዲስ የግብርና ቴክኖሎጂዎችን አጋር አካላት በቅርበት በመገምገም ከሰርቶ ማሳያ ወጥተው የአርሶ አደሩን ህይወት ሊቀይሩ ወደሚችሉ አሰራሮች ሊያሸጋግሯቸው እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡

በመስክ  በዓሉ ላይ አርሶ አደሮች፣ ተመራማሪዎች፣ የግብርና ባለሙያዎችና በየደረጃው የሚገኙ አመራሮች ተሳታፊ ነበሩ፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም