ለኢዶ ሴሩፍታ ወርቃ 73 ኪሎ ሜትር የአስፋልት መንገድ የመሠረት ድንጋይ ተቀመጠ

134

ሐዋሳ  ታህሳስ 22/2011በምዕራብ አርሲ ዞን ከኢዶ ሴሩፍታ ወርቃ የሚወስደውን 73 ኪሎ ሜትር የአስፋልት መንገድ ለመገንባት የመሠረት ድንጋይ ተቀመጠ፡፡

በአራት ዓመታት ጊዜ ውስጥ ለሚጠናቀቀው መንገድ ግንባታ መንግሥት 1 ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር በጀት መድቦለታል።

መንገዱ እናቶችና ሕሙማን ለወሊድና ለሕክምና ወደ ጤና ተቋማት ሲጓዙ ይደርስ የነበረውን  ሞት እንደሚያስቀርና  ምርታቸው ለገበያ በማቅረብ ተጠቃሚ እንደሚያደርጋቸው ኢዜአ ያነጋገገራቸው የአካባቢው ነዋሪዎች ገልጸዋል፡፡

የመሠረት ድንጋዩንያስቀመጡት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ እንደተናገሩት መንገዱ የአካባቢውን የግብርና ምርትና የተፈጥሮ ሀብት አልምቶ ለገበያ ለማቅረብ ፋይዳው ከፍተኛ ነው፡፡

የአካባቢው ኅብረተሰብ ለረጅም ዓመታት መንገዱ እንዲገነባለት ሲጠይቅ እንደነበር ያስታወሱት ሚኒስትሩ፣ የመሠረት ድንጋይ መጣሉ ለአካባቢው ልማት መንግሥት የሰጠውን ትኩረት ያሳያል ብለዋል፡፡

በከፍተኛ ሁኔታ ቡናን ከሚያመርቱ የኦሮሚያ ወረዳዎች አንዱና ትልቁ መሆኑን የተናገሩት ሚኒስትሩ  መንገድ ባለመኖሩ በተለይ ክረምት ወደዚህ ከተማ መግባት አይቻልም ነበር ብለዋል።

መንገዱ የባሌና ቦረና አካባቢዎችና ከደቡብ ክልል ስለሚያገናኝ ሕዝቡ የተሰማውን ደስታ እንደገለጸ ሁሉ ግንባታው እስኪጠናቀቅ ድጋፍ እንዲያደርግም አሳስበዋል፡፡

የኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ኢንጅነር ሐብታሙ ተገኝ እንዳሉት መንገዱ ለኅብረተሰቡ ከሚሰጠው ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ባለፈ፤ በግንባታው ወቅት ለአካባቢው ኅብረተሰብ ሥራ እንደሚፈጥር ተናግረዋል፡፡

የመንገዱ ግንባታ በታሰበለት ጊዜ እንዲጠናቀቅ ተቋራጩ መሣሪያዎችን በፍጥነት በማስገባት ሥራውን መጀመር እንዳለበት ጠቁመው ባለሥልጣኑ ክትትል እንደሚያደርግ ተናግረዋል፡፡

የአካባቢው ኅብረተሰብና የመንግሥት አካላትም መንገዱ በተያዘለት ጊዜ ገደብ እንዲጠናቀቅ ድርሻቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል።

በነንሰቦ ወረዳ የወርቃ ከተማ ነዋሪ የሆኑት አቶ ለማ መንግሥቱ እንዳሉት መንገዱ በክረምት አገልግሎት ስለማይሰጥ ዝናብ ሲጥል ነፍሰጡር እናቶችና ሕሙማንን ወደ ዶዶላ ለወሊድና ለሕክምና ለማድረስ እንቸገራለን ብለዋል፡፡

መንገዱ እንዲሰራላቸው ሲጠይቁ መቆየታቸውን ያስታወሱት አስተያየት ሰጪው፣ ጥያቄያቸው ምላሽ አግኝቶ ለመንገዱ ግንባታ የመሠረት ድንጋይ ሲጣል ማየታቸው እንዳስደሰታቸውም ገልጸዋል፡፡

ሌላዋ የከተማዋ ነዋሪ ወይዘሮ ቀመሪያ አደም በበኩላቸው መንገዱ በተለይ የሴቶችን ሕይወት ከባድና ፈተና የበዛበት እንዳደረገው ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ሳምሶን ወንድሙ መንግሥት ከፍተኛ የትራፊክ ፍሰት ያላቸውን ነባር የገጠር ጠጠር መንገዶችን ደረጃ እያሳደገ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የመንገዱ ግንባታ የሚከናወነው በአገር በቀሉ ጎንድዋና ኢንጅነሪንግ አማካሪነትና በዓለማየሁ ከተማ ጠቅላላ ተቋራጭ መሆኑንም ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም