ፍርድ ቤቱ በኮሎኔል ጉደታ ኦላና ላይ ፖሊስ የጠየቀውን ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ፈቀደ

100

አዲስ አበባ ታህሳስ 22/2011 የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 10ኛ የወንጀል ችሎት በኢትዮ-ቴሌኮም የሴኪዩሪቲ ዲቪዥን ሃላፊ ኮሎኔል ጉደታ ኦላና ላይ ፖሊስ የጠየቀውን ተጨማሪ የ14 ቀን የምርመራ ጊዜ ፈቀደ።

ተጠርጣሪው ግለሰብ ኮሎኔል ጉደታ ኦላና ህዳር 6 ቀን 2011 ዓ.ም በብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን የስራ ኃላፊዎች ላይ ምርመራ በሚያደርጉ የዐቃቤ ህግና ፌዴራል ፖሊስ አባላት ላይ ዛቻና ማስፈራራት በማድረግ የምርመራ ሂደቱን አደናቅፈዋል በሚል ነበር የተያዙት።

ፖሊስ ለፍርድ ቤቱ በኮሎኔል ጉደታ ኦላና ዙሪያ የሚሰራቸው ቀሪ ስራዎች እንዳሉት በመግለጽ የተጨማሪ የ14 ቀን ፈቃድ እንዲሰጠው ጠይቋል።

የተጠርጣሪ ተከላካይ ጠበቆች በበኩላቸው ፖሊስ የጠየቀው ተጨማሪ የጊዜ ቀጠሮ አግባብነት የለውም ብለው ተከራክረዋል።

ፍርድ ቤቱ የግራ ቀኙን ክርክር ካዳመጠ በኋላ ፖሊስ የጠየቀውን የ14 ቀን ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ፈቀዷል።

ኮሎኔል ጉደታ መጀመሪያ ከተጠረጠሩበት ወንጀል በተጨማሪ በምርመራ ሂደት ፖሊስ ”ከገቢያቸው በላይ ምንጩ ያልታወቀ ሀብት በቤተሰባቸው ስም አካብተዋል፣ በሙስና ያገኙትን ገንዘብም ሕጋዊ በማድረግ ወንጀል ጠርጥሬያቸዋለሁ” በሚል ከዚህ በፊት ለፍርድ ቤቱ አቅርቦ እንደነበርም ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም