በጌዴኦ ዞን በትምህርት ቤቶች የሚታየው የግብአት እጥረት በትምህርት ጥራት ላይ ተፅዕኖ እያሳደረ መሆኑ ተገለፀ

177

ዲላ ታህሳስ 22/2011 በጌዴኦ ዞን በሚገኙ ትምህርት ቤቶች የሚታየው የግብአት መጓደል በትምህርት ጥራት ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ እያሳደረ መሆኑን ርዕሳነ መምህራን ገለፁ ፡፡

የዞኑ ትምህርት መምሪያ በየትምህርት ቤቶች በሚታዩ ችግሮች ዙሪያ ከትምህርት ኃላፊዎችና ባለለድርሻ አካላት ጋር ትናንት በዲላ ከተማ የምክክር መድረክ አካሂዷል ፡፡

በምክክር መድረኩ የአመራር አካላት ክፍተት፣ የአመለካከት፣ የመጻሕፍት፣ የመማሪያ ክፍሎች፣ የቤተ ሙከራ ቁሳቁሶችና ሌሎች ችግሮች በትምህርት ጥራት ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ እያሳደረ መሆኑን ተገልጿል፡፡ 

የይርጋጨፌ ሁለተኛ ደረጃና መሰናዶ ትምህርት ቤት ርዕሰ መምህር ንጉሴ ሌጌ እንደተናገሩት ትምህርት ቤቱ በርካታ ማሻሻዎች እያደረገ ቢሆንም ከአቅሙ በላይ የሆኑ ችግሮች ግን በትምህርት ጥራት ላይ ተጽእኖ እያሳደሩ ነው፡፡

በትምህርት ቤቱ የመጽሐፍት እጥረት ባለባቸው የትምህርት አይነቶች አንድ መጽሐፍ ለሶስትና ከዚያ በላይ  ተማሪዎች እንዲገለገሉበት እየተደረገ ነው፡፡

ከ3 ሺህ 600 ተማሪዎች በላይ እያስተናገደ በሚገኘው በዚህ ትምህርት ቤት ውስጥ በክፍል እጥረት ምክንያት እስከ 90 ተማሪዎች በአንድ ከፍል ውስጥ በተጨናነቀ ሁኔታ እንዲማሩ እየተደረገ ነው፡፡

እነዚህና ሌሎች ለትምህርት የሚያስፈልጉ ግብአቶች አለመሟላት የትምሀርት ጥራትን ለማስጠበቅ በሚደረገው ጥረት ላይ ማነቆ ሆነዋል ፡፡

በዚህም ምክንያት ''ትምህርት ቤቱ በ2010 የትምህርት ዘመን በ10ኛና 12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተናዎች ያስመዘገበው ውጤት ዝቅተኛ እንዲሆን አድርጎታል'' ብለዋል፡፡

''በዘንድሮው የትምህርት ዘመን ይህን ውጤት ለመቀየር ጉድለቶቻችንን ገምግመን ወደ ስራ ገብተናል'' ያሉት ርዕሰ መምህሩ የተለያዩ የማሻሻያ እርምጃዎችን መውሰዳቸውን ገልፀዋል ፡፡

በኮቾሬ ወረዳ የብሎያ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ርዕሰ መምህር ማሙሽ ሮቤ በበኩላቸው ባለፈው ዓመት ከተገመገሙ ችግሮች መካከል ለትምህርት ቤቱ የሚመደበው በጀት በወቅቱ አለመድረስ ተጠቃሽ ነው፡፡

እንደ ርዕሰ መምህሩ ገለፃ ለተለያዩ ግብአቶች ማሟያ የሚሆነው ይኸው በጀት ዘንድሮም ለየትምህርት ቤቱ እስካሁን አልደረሰም ፡፡

በዚህም የተነሳ ትምህርት ቤቱ የጽሕፈት መሳሪያ ግዢ ባለመፈፀሙ መምህራን አመታዊም ሆነ ሳምንታዊ የማስተማሪያ ዕቅድ ሳያወጡ ወደ ሥራ በመግባታቸው በትምህርት ጥራት ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ እሳደረ ነው ፡፡

የመምህራን ምደባ በጊዜ አለመከናወኑም በተወሰኑ የትምህርት አይነቶች ላይ ክፍተት መፍጠሩንና የትምህርት ስራውን እያስተጓጎለ መሆኑን ገልጸዋል ፡፡

የጌዴኦ ዞን ምክትል አስተዳዳሪና የትምህርት መምሪያ ኃላፊ አቶ ተካልኝ ታደሰ በዞኑ ትምህርት ቤቶች የሚታዩ ችግሮችን ለማሻሻል ባለድርሻ አካላት የየራሳቸውን የመፍትሔ እርምጃ እንዲወስዱ ለማድረግ ውይይት  መደረጉን ተናግረዋል ፡፡

በውይይቱም በትምህርት ጽህፈት ቤቶች፣ ሱፐርቫይዘሮችና በርዕሳነ መምህራን በኩል የታዩ ክፍተቶች መገምገማቸውን ገልፀው በመንግስት ደረጃም ያሉ ጉድለቶች መፈተሹን አስታውቀዋል፡፡

በተለይ በትምህርት ቤቶች ውስጥ ያሉ ጉድለቶችን ለማሟላት ህብረተሰቡን ከማሰተባበር ባለፈ ከፍተኛ ሀብት ከመመደብ፣ ለትምህርት ቤቶች የሚያግዙ ግብዓቶችን በወቅቱ እንዲደርስ ከማድረግ አኳያ ክፍተቶች መስተዋላቸውን አስረድተዋል ፡፡

''በዞኑ ያለውን የመማሪያ ክፍሎች እጥረት ለመቅረፍ 800 ክፍሎችን መገንባት ያስፈልገናል'' ያሉት አቶ ተካልኝ በአንዳንድ ትምህርት ቤቶች  በአንድ ክፍል ከ100 በላይ ተማሪዎች እንደሚማሩ ተናግረዋል፡፡

የመማሪያ ክፍሎችን ችግር በዘላቂነት ለመፍታት የዞኑ አስተዳደር የተለያዩ የትምህርት ቤት ግንባታ ፕሮጀክቶችን ቀርፆ ተግባራዊ ለማድረግ እየተንቀሳቀሰ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

በህብረተሰቡ ድጋፍና በአስተዳደሩ እየተሰሩ ላሉ የማስፋፊያ ሥራዎች መምሪያው 3 ሚሊዮን ብር መመደቡን አብራርተዋል ፡፡

በአካባቢው በነበረ የፀጥታ ችግር ምክንያት የወደሙ አራት ትምህርት ቤቶችን መልሶ ለመገንባት የሚያስችል ድጋፍ ደግሞ ከደቡብ ክልል ትምህርት ቢሮ ማግኘታቸውን ገልፀዋል፡፡

''በዞን ደረጃ የተማሪ መጽሐፍ ጥምርታ አንድ ለሶስት ነው'' ያሉት አቶ ተካልኝ በአንዳንድ የትምህርት አይነቶች ደግሞ አንድ መጽሐፍ ለ16 ተማሪዎች የሚዳረስባቸው ትምህርት ቤቶችም መኖራቸውን ጠቁመዋል ፡፡

ኃላፊው የመጻሕፍት ችግርን ለመፍታትም ከክልል ትምህርት ቢሮ ጋር እየሰሩ እንደሚገኙ ጠቁመዋል፡፡

ጊዜያዊ መፍትሔ ለማበጀት ደግሞ ከ1ኛ እስከ 12ኛ ክፍል ያሉ መጻሕፍት በየትምህርት ቤቱ በ“ፍላሽ ” እንዲደርስ በማድረግ ኮምፒውተር ባለባቸው ትምህርት ቤቶች ተማሪዎች የሚፈልጉትን መጽሐፍ እንዲያገኙ የማመቻቸት ሥራ እየተከናወነ እንደሚገኝ አስረድተዋል ፡፡

በትምህርት ቤቶች ውስጥ ያለውን የቤተ ሙከራ ቁሳቁስ ጉድለት ለማሟላትም መምሪያው ከመደበው 300 ሺህ ብር በተጨማሪ ከዲላ ዩኒቨርስቲ ጋር በመተባበር “ ስቴምስ ኢነርጂ ” ከተሰኘ ግብረ ሰናይ ድርጅት አንድ ነጥብ አምስት ሚሊዮን ብር የሚገመት የቁሰቀቁስ ድጋፍ መገኘቱን አብራርተዋል ፡፡

በትምህርት ሥራው ላይ የሚያስፈልጉ ግብአቶችን ለማሟላት በዞኑ አስተዳደርም ሆነ በህብረተሰቡ ትብብር ከሚሰሩ ስራዎች በተጨማሪ ከተለያዩ ተቋማትና ግብረሰናይ ድርጅቶች ጋር ቅንጅት በመፍጠር እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በምክክር መድረኩ ላይ የዞን ፣ የወረዳና የከተማ አስተዳደር አመራር አካላት እንዲሁም የተለያዩ የትምህርት ሥራ ኃላፊዎች እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል ፡፡  

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም