በምስራቅ ጎጃም ዞን 70 ሺህ ሄክታር መሬት በመስኖ እየለማ ነው

68

ደብረማርቆስ ታህሳስ 22/2011 በምስራቅ ጎጃም ዞን በተያዘው የበጋ ወቅት 70 ሺህ ሄክታር መሬት በመጀመሪያ ዙር በዘመናዊና ባህላዊ መስኖ እየለማ መሆኑን የዞኑ ግብርና መምሪያ አስታውቀ።

የመምሪያው የመስኖ ልማት ባለሙያ አቶ አያሌው ገሌ ለኢዜአ እንደገለጹት በተያዘው የበጋ ወቅት የከርሰና የገጸ ምድርን ውሃ በመጠቀም 138 ሺህ ሄክታር መሬት ለማልማት ታቅዶ እየተሰራ ነው።

እስካሁን በተደረገው እንቅስቃሴ 60 ሺህ ሄክታር መሬት በዘመናዊ መስኖ የለማ ሲሆን 10 ሺህ ሄክታሩም በባህላዊ መንገድ በአርሶ አደሮች በመልማት ላይ መሆኑን አመልክተዋል።

በመስኖ እየለሙ ካሉት መካከል አትክልት፣ ቅመማ ቅመም  ፣ አዝርዕትና የጥራጥሬ ሰብሎች እንደሚገኙበት ገልጸው በልማቱ 140 ሺህ የሚደርሱ አርሶ አደሮች በመሳተፍ ላይ መሆናቸውን ተናግረዋል።

እንደ አቶ አያሌው ገለጻ በዕቅድ የተያዘውን ለማሳከት ቀሪው ሄክታር መሬት ሙሉ በሙሉ በሰብል ለመሸፈን የእርሻ ሥራው ተጠናክሮ ይቀጥላል።

ምርታማነትን ለማሳደግም ከ72 ሺህ ኩንታል በላይ ማዳበሪያ፣ 40 ሺህ ኩንታል የተፈጥሮ ማዳበሪያ እንዲሁም 12 ሺህ ኩንታል ምርጥ ዘር ተሳታፊ አርሶ አደሮች መጠቀማቸውን ገልፀዋል።

በተያዘው የበጋ ወቅት በመስኖ ልማት ለማልማት ከታቀደው ማሳ ከ21 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ለማግኘት መታቀዱንም ባለሙያው አስታውቀዋል።

በልማቱ እየተሳተፉ ካሉ አርሶ አደሮች መካከል የአዋበል ወረዳ የወጀል ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ስዩም ካሴ በመስኖ ልማት በዓመት እስከ ሦስት ጊዜ እያለሙ መሆናቸውን ገልጸዋል።

"ባለፈው ዓመት በመስኖ ካለማሁት የአትክልት ሽያጭ 30 ሺህ ብር ገቢ አግኝቺያለሁ" ብለዋል።

በተያዘው የበጋ ወቅትም በመኽር ወቅት በባቄላ ሸፍነውት የነበረውን መሬት በወቅቱ በመሰብሰብ በግማሽ ሄክታር መሬት ላይ ሽንኩርት እያለሙ መሆናቸውን ተናግረዋል።

በግማሽ  ሄክታር ማሳ  ላይ አብሽ፣ ቃሪያና ጎመን በመስኖ እያለሙ መሆኑን የገለጹት ደግሞ በአነደድ ወረዳ የነችፎ ቀበሌ ነዋሪ ወይዘሮ አዛውንት ይበልጣል ናቸው።

የመስኖ ልማት ሥራ ከመጀመራቸው ስድስት ዓመት በፊት ልጆቻቸውን ለማሳደግ ይቸገሩ እንደነበር አስታውሰው፣ ጎረቤቶቻቸውን አይተው የጀመሩት የመስኖ ልማት ሥራ ተጠቃሚ እንዳደረጋቸው ገልጸዋል።

የመስኖ ልማት ሥራ ከጀመሩ ከአምስት ዓመት ወዲህም በአብዛኛው አብሽ እና ጥቁር አዝሙድ በማልማት በዓመት ከ40 ሺህ ብር በላይ እያገኙና በእዚህም ልጆቻቸውን ያለችግር በማስተማር ላይ መሆናቸውን ተናግረዋል።

"ዘንድሮም አሁን እያለሙት ያለውን ጨምሮ በሁለቱ ዙር ከ50 ሺህ ብር በላይ ገቢ አገኛለሁ ብዬ እጠብቃለሁ" ብለዋል።

በዞኑ ባለፈው ዓመት በአንደኛና በሁለተኛ ዙር በመስኖ ከለማው መሬት ከ17 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት መገኘቱ ታውቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም