ምክር ቤቱ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጋር በጥምረት ሊያሰራው የሚያስችለውን የመግባቢያ ስምምነት ተፈራራመ

105

አዲስ አበባ ታህሳስ 22/2011 የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጋር በጥምረት ሊያሰራው የሚያስችለውን የመግባቢያ ስምምነት ተፈራራመ።

የመግባቢያ ስምምነቱ በዋናነት በፖሊሲዎች፣ በህጎች፣ ደንቦች፣ መመሪዎችና በልዩ ልዩ ንግድ ነክ ተግዳሮቶች ዙሪያ መፍትሄ አመንጪ ሀሳቦችን ለማፍለቅና በዕቅዶች ዙሪያ በጋራ ለመስራት ያለመ ነው።

የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ወይዘሮ መሰንበት ሸንቁጤ እንደገለጹት የንግዱ ማህበረሰብ የሚያደርጋቸውን የንግድ እንቅስቃሴዎች በዘመናዊ አሰራርና ስርዓት ማገዝ የአገርንና የመንግስትን ህልውና ለማስጠበቅ ወሳኝ ሚና አለው።

በተለይም ምክር ቤቱ ከዚህ በፊት በመንግስት በኩል የሚወጡትን አዋጆችና ደንቦች ላይ ከወጡ በኋላ አስተያየት ይሰጥ የነበረውን በስምምነቱ መሰረት ግን አዋጆቹና መመሪያዎቹ ከመውጣታቸው በፊት ተገቢውን አስተያየት ለመስጠት እንደሚያግዝ ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ እያደገ የመጣው የግሉ ዘርፍ እንቅስቃሴ፣ አገሪቷ የዓለም አቀፉ የንግድ ድርጅት አባል ለመሆን የምታደርገው ጥረትና የአገሪቷ ንግድ በአለም አቀፍ  ደረጃ ተወዳዳሪ እንዲሆን ከዩኒቨርሲቲው ጋር ተቀራርቦ መስራት ያስፈልጋል።

በአሁኑ ወቅት ምክር ቤቱ ከ17 ሺህ በላይ አባላት እንዳሉት ፕሬዝዳንቷ ጠቅሰው በአሁኑ ወቅት እየመጡ ያሉትን አዳዲስ አባላትንም ተወዳዳሪ እንዲሁኑ በስልጠና ለማገዝ ጭምርም ስምምነቱ ተደርጓል ሲሉም ተናግረዋል።

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ፕሮፌሰር ጣሰው ወልደሃና በበኩላቸው ዩኒቨርሲቲው ከመማር ማስተማር በተጓዳኝ የማህበረሰቡን ችግር ሊፈቱ የሚችሉ የጥናትና የምርምር ስራዎቹን እየሰራ ይገኛል።

በዛሬው እለት የተፈረመው ስምምነትም ዩኒቨርሲቲው ለንግዱ ማህበረሰብ የሙያና የልምድ ስልጠና፣ በስራ ፈጠራ፣ በህይወት ክህሎትና በወደፊት የቢዝነስ ሞዴል፣ ቴክኖሎጂ መር አመራርና አለም አቀፍ ቢዝነስ ቅንጅት ላይም በጋራ ለመስራት ያስችላል።

በተለይም የስምምነቱ ሰነድ ትኩረት የሚደረግባቸውን መስኮች በዝርዝር ለይቶ በጋራ ለመስራት እንደሚያግዝ ጠቅሰው ይህም ዩኒቨርሲቲው እስካሁን ከሚሰጠው በእውቀት ላይ የተመሰረተ ትምህርት በማሻሻል እውቀትና ክህሎትን አቀናጅቶ ለማስተማር ያስችላል ሲሉም ጠቅሰዋል።

የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት የተመሰረተበትን 71ኛ ዓመት ለማክበር በዝግጅት ላይ ይገኛል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም