ባልተፈለጉ መልእክቶች ሳቢያ የሞባይል መልዕክት አገልግሎት መጠቀም አቁመናል - የአዲስ አበባ ነዋሪዎች

122

ታህሳስ 21 /2011 ኢትዮ ቴሌኮም ከሚሰጣቸው አገልግሎቶች መካከል  የጽሑፍ መልዕክት አንዱ ቢሆንም  በማይፈልጉዋቸው መልእክቶች መብዛት ሳቢያ አገልግሎቱን በአግባቡ መጠቀም አለመቻላቸውን  አስተያየታቸውን የሰጡ  የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ተናገሩ፡፡

በአገልግሎቱ የሰውን የግል መብቶች የሚጋፉ፣ ያልተፈለጉ፣ ጊዜና ገንዘብን የሚያባክኑ መልዕክቶች መበራከታቸው አገልግሎቱን በአግባቡ እንዳይጠቀሙ ምክንያት በመሆኑ የጽሁፍ መልዕክትን ለማቋረጥ እንደተገደዱም ነው ነዋሪዎች የሚናገሩት፡፡

በጉለሌ ክፍለ ከተማ አዲሱ ገበያ አካባቢ ነዋሪ ወጣት አማረ ክንፉ እንደተናገረው ከዚህ በፊት የሞባይል መልዕክት አገልግሎት ይጠቀም እንደነበርና ከበርካታ ጓደኞቹ ጋር መረጃ በመለዋወጥ በአነስተኛ ሂሳብ  ይጠቀም ነበር፡፡

ይሁንና ከሁለትና ሶስት ዓመታት ወዲህ ባልተገባ ሁኔታ የሚለቀቁ የመልእክት አገልግሎቶች ሰዓት እንኳን ሳይመርጡ በብዛት በመላካቸው መልዕክቱን ላለማየትና አሰልቺ በመሆናቸው ጭምር ከጓደኞቹ ጋር መረጃን በጽሑፍ መጠቀም ማቆሙን ተናግሯል፡፡

በየካቲት 12 ከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት አካባቢ ነዋሪ  አቶ ባጫ ለሚሳ በበኩላቸው ኢትዮ ቴሌኮም ከሚሰጣቸው አገልግሎቶች መካከል የመልእክት መላላኪያ አንዱና አስተማማኝ ቢሆንም የማይፈልጓቸው መልዕክቶች በብዛት እየመጡ አገልግሎቱን በማጨናነቅ በተገቢው መንገድ እንዳይጠቀሙ ማድረጉን  ነው የጠቆሙት፡፡

ህገወጥ ሆነው በህጋዊው ተቋም ሁሉ በዚህ መልዕክት ይህን ሽልማት ያገኛሉ በማለት በተለይ የማያውቀውን ህብረተሰብ የሚበዘብዙ አካላትን መቆጣጠር ይገባል ያሉት አቶ ባጫ፤ ቴሌ ይህን እያ ዝም ማለት የለበትም ሲሉ አስተያታቸውን ሰጥተዋል፡፡

አስፈላጊና አስቸኳይ መልእክቶች ቢደርሱ እንኳ በብዛት በሚመጡ ያልተገቡ መረጃዎች ሳቢያ መዘናጋትን እንደሚፈጥሩ የተናገሩት ደግሞ የኮከበ አፅባህ ትምህርት ቤት መምህር አቶ ኢያሱ ያረጋል፤ ህብረተሰቡ በገዛ ሀብቱና ንብረቱ ተጠቃሚ እንዳይሆን አድርጎታል ይላሉ፡፡

በኢትዮጵያ ብሄራዊ ሎቶሪ አስተዳደር የህዝብግኑኙነት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ቴዎድሮስ ንዋይ በበኩላቸው በሀገሪቱ በእጣ እና በእድል ዙሪያ የሚሰሩ ድርጅቶች ለማህበራዊ አገልግሎቶች የሚያበረክቱት አስተዋጽኦ እየታየ በአስተዳደሩ ፍቃድ እንደሚሰጥ ተናግረዋል፡፡

የመቆዶኒያ የወጣቶች ማህበር እና የተክለ ብአዴን ማህበር የመሳሰሉት ከድርጅቱ ፍቃድ አግኝተው የሚንቃሳቀሱ መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡

በህገወጥ መንገድ እጣ እና እድል ይዘው የሚሰሩ አካላትን ከኢትዮ ቴሌኮም ጋር በመቀናጀት እርምጃ እንደሚወስድም ተናግረዋል፡፡

ለአብነት በ8143 እና በ8154 የመልእክት አገልግሎት ሲጠቀም የተደረሰበት ድርጅት ላይ እርምጃ እንዲወሰድ ለኢትዮ ቴሌ ኮም ቢያሳውቁም እርምጃ ባለመወሰዱ በሚዲያ ጭምር እየተቀሰቀሰ ተገቢ ያልሆነ ስራ እተየሰራ መሆኑን አቶቴ ዎድሮስ አስረድተዋል፡፡

በኢትዮ ቴሌኮም የኮሙዩኒኬሽን ኤክስኪዩቲቭ ዳይሬክተር ወይዘሪት ጨረር አክሊሉ ስለጉዳዩ ተጠይቀው የህብረተሰቡ ጥያቄ ተገቢ መሆኑንና በተለያየ መንገድም ለተቋማቸው ሲያሳውቅ መቆየቱንም ተናግረዋል፡፡

ኢትዮ ቴሌኮም ህብረተሰቡ የማይፈልጋቸውን መልእክቶች አቁም! በሚል መረጃ በመጠቀም መልእክቱ እንዳይደርሰው የሚያደርግበት አሰራር መዘርጋቱንና በቅርቡ ስራ እንደሚያስጀምርም ጠቁመዋል፡፡

ባልተገባ መንገድ የእጣ አገልግሎት ለመስጠት የሚንቀሳቀሱ ድርጅቶችን ከብሄራዊ ሎቶሪ ጋር በመቀናጀት ቁጥጥር እንደሚደረግ የጠቆሙት ወይዘሪት ጨረር አሁንም ያሉ መስመሮችን በመከታተል እርምጃ እንደሚወሰድም አብራርተዋል፡፡  

የአጭር መልዕክት አገልግሎት አሁን ከሚስተዋልበት ችግር ባለፈ ጠቀሜታው ከፍተኛ መሆኑን የተናገሩት ዳይሬክተሯ ለበርካታ ማህበራዊ አገልግሎቶች የሰጠው ጥቅምም ቀላል አለመሆኑን አስረድተዋል፡፡

ማህበራዊ አገልግሎትን ከማሳደግ ጋር ተያይዞ ለመቆዶኒያ አረጋዊያንና የአዕምሮ ህሙማን መርጃ ድርጅት በተከፈተው የአጭር መልዕክት አገልግሎት  ከ74 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ መደረጉንም ነው ዳይሬክተሯ የጠቀሱት፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም