አስተዳደሩ ለችግር የተጋለጡ አረጋውያን ዕውቀታቸውንና ልምዳቸውን ጥቅም ላይ እንዲያውሉ ይደግፋል-ከንቲባ ኢብራሂም

48

ድሬዳዋ ታህሳስ 21/2011 የድሬዳዋ አስተዳደር ለችግር የተጋለጡ አረጋውያንን በቋሚነት በመደገፍ የካበተ ዕውቀታቸውንና ልምዳቸውን ጥቅም ላይ እንዲያውሉ ድጋፍ እንደሚያደርግ ከንቲባ ኢብራሂም ዑስማን አስታወቁ።

''እየሮጥን አረጋውያንን እንደግፍ!'' በሚል መሪ ሃሳብ ዛሬ በድሬዳዋ የጎዳና ላይ ሩጫ ተካሂዷል፡፡

በሩጫው  በሁሉም የዕድሜ ክልል የሚገኙ ነዋሪዎች፣አመራሮችና አርቲስቶች ተሳትፈዋል፡፡

ከንቲባው ሩጫውን ባስጀመሩበት ወቅት እንዳመለከቱት አስተዳደሩ አዛውንቶቹ ለዘመናት ያከማቹት ዕውቀትና ልምድ በሥራ ላይ እንዲያውሉ እገዛ ያደርጋል፡፡

አስተዳደሩ ለዳዊት አረጋውያን በጎ አድራጎት ማህበር በሰጠው አምስት ሺህ ካሬ ሜትር ቦታ የተጀመረው ማዕከል ዕውን እንዲሆን ይረዳል ብለዋል። 

ማህበሩ ጧሪ ቀባሪ ያጡ አዛውንቶች በቋሚነት ለመደገፍ እያከናወነ የሚገኘው ሥራ አበረታች መሆኑንም  መስክረውለታል፡፡

ከተሳታፊዎቹ አንዳንዶቹ ለኢዜአ እንደተናገሩት ጧሪ ቀባሪ አጥተው በየስርቻው የወደቁ አዛውንቶችን በቋሚነት ለመደገፍ በዕውቀታቸው፣ በጉልበታቸውና በገንዘባቸው ድጋፍ ያደርጋሉ፡፡

በሩጫው ላይ የተሳተፈችው የምስለእናት አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የሰባተኛ ክፍል ተማሪ ኤልሳ ሰለሞን በትምህርት ቤት  ባቋቋሙት የተማሪ ማህበራት ገንዘብና ልብስ እያሰባሰቡ በበዓላት ወቅት  አዛውንቶችን እንደሚደግፉ ተናግራለች ፡፡

የተቸገሩ አዛውንቶችን መደገፍ ልባዊ  ደስታ ይሰጠኛል ብላለች፡፡

እስከ 10ሺ የሚገመቱ ነዋሪዎች የተሳተፉበትን ሩጫ ያሸነፉት አቶ ገዛኸኝ አበራ ችግረኛ አዛውንቶች በመደገፍ ግንባታው ለተጀመረው ማዕከል ሁሉም ድጋፉን እንዲሰጥ ጠይቀዋል፡፡

''እየሮጡ መደገፍ  መልካም ነው፤ በቀጣይ ገቢ ማሰባሰቢያ ቴሌቶንና ባዛር ማዘጋጀትና የተሻለ ገቢ የመሰብሰብ ሥራ ሊሰራ ይገባል'' ብለዋል፡፡

ወይዘሮ ኢፍቱ አህመድ የተባሉ ተሳታፊ በበኩላቸው በሃፎሻዎች፣ በእድሮችና ባህላዊ አደረጃጀቶች ለማዕከሉ ግንባታ አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ ማድረግ እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡

በማህበሩ  ድጋፍ እያገኙ ያሉት አዛውንት አቶ መሐመድ ዓሊ ኅብረተሰቡ ለሚያደርግላቸው ድጋፍ አመስግነው፣ በቋሚነት የሚጠለሉበት ማዕከል ተገንብቶ ሲጠናቀቅ ከጎዳና ኑሮ እንደሚገላገሉ ጠቁመዋል፡፡

የአስተዳደሩ ነዋሪዎች ለማዕከሉ ግንባታ ድጋፍ  እንዲያደርጉ ጠይቀዋል፡፡

ለአሸናፊዎቹ የተዘጋጀውን ሜዳሊያና ዋንጫ ታዋቂ የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች ከድሬዳዋ አስተዳደር ወጣቶችና ስፖርት ኮሚሽነር ከድር ጁሃር ጋር በመሆን ሽልመዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም