በደብረ ብርሃን ከተማ በ10 ሚሊዮን ዶላር ወጪ የአዳሪ ትምህርት ቤት ግንባታ ተጀመረ

80

ደብረብርሃን ታህሳስ 21/2011 በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትዉልደ ኢትዮጵያውያን ለአገሪቱ መሠረታዊ ለውጥ በሚበጁ የልማትሥራዎች የሚያደርጉት ተሳትፎ እያደገ መምጣቱን የአማራ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ ገለጹ።

በደብረ ብርሃን ከተማ ኢትዮጵያ ኢዱኬሽን ኢኒሸቲቭ ኢን ኮርፖሬሽን በ10 ሚሊዮን ዶላር ወጪ የ "ኃይሌ ማናስ አካዳሚ አዳሪ ትምህርት ቤት'' ግንባታን አስጀምሯል።

የግንባታውን ጅማሬ አስመልክቶ ዛሬ በክልሉ ከፍተኛ የሥራ አመራሮች አማካኝነት የመሠረት ድንጋይ ተቀምጧል።

በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የቢሮው ኃላፊ አቶ ንጉሱ ጥላሁን እንደተናገሩት አሁን በአገሪቱ ካለው የፖለቲካ ለውጥ ጋር ተያይዞ ወደ አገር በመመለስ ልማቱን የሚደግፉ ዜጎችና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ተሳትፎ ጨምሯል።

በተለይ ደግሞ  በትምህርት ዘርፍ አዲስ ትዉልድ ለመቅረጽና የትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅ የሚያደርጉት ተሳትፎ መዋቅራዊ ለውጥ ለማምጣት ጠቀሜታ እንዳለው አመልክተዋል።

በአሜሪካ የሚኖሩ ትውልደ ኢትዮጵያውያን ባቋቋሙት ”ወንፈል” በሚባል ድርጅት አማካኝነት በባህርዳርና በጎንደር ከተሞች የትምህርት ተቋማት ለማስገንባት በእንቅስቃሴ ላይ መሆናቸውን ለአብነት አንስተዋል።

የትምህርት ቤቶቹ ግንባታ ዓለም አቀፍ ደረጃን የጠበቀ ስለሚሆን የአገሪቱን የትምህርት ሥርዓት ለማሻሻልና  መምህራን ልምድ የሚቀስሙበት እንደሚሆን እምነታቸውን ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ ኢዱኬሽን ኢኒሸቲቭ ኢን ኮርፖሬሽን ምክትል ዳይሬክተር አቶ ተስፋዬ ክፍሌ በከተማው ግንባታው የሚካሄደው የአገሪቱን የትምህርት ጥራት በማሻሻል ሂደት አስተዋጽኦ ለማድረግ መሆኑን አስረድተዋል።

የከተማው አስተዳደር በሰጣቸዉ 80ሺህ ካሬሜትር መሬት ላይ በመጀመሪያ ዙር 13ሕንፃዎች ግንባታ መጀመሩንና የሁለተኛው ዙር 11ሕንፃዎች ግንባታ ደግሞ በመጪዉ ዓመት እንደሚጀመር ተናግረዋል።

ከሕንፃዎቹ መካከል የመማሪያ፣ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ቤተ ሙከራዎች፣የተማሪዎችና መምህራን መኖሪያዎችና ጅምናዚዬም ይገኙባቸዋል።

የትምህርት ቤቱ ግንባታ ሲጠናቀቅ ከመላው አገሪቱ የተሻለ ውጤት ያላቸውን 400 ተማሪዎች እንደሚቀበልም አቶ ተስፋዬ አስታውቀዋል።በ2013 የመጀመሪያዎቹን 100 ተማሪዎችን ይቀበላል ብለዋል።

ትምህርት ቤቱም በዓለም አቀፍ የትምህርት ቤቶች ደረጃ  መሠረት በአንድ ክፍል 25 ተማሪዎች እንደሚያስተናግድና ከዘጠነኛ እስከ 12ኛ ክፍሎች እንደሚያስተምር ዳይሬክተሩ አስረድተዋል።

ግንባታዉን የሚያከናውነው የራማ ኮንስትራክሽን ድርጅት ሥራ አስኪያጅ አቶ ዘላለም አያሌው በበኩላቸዉ ግንባታው በተያዘለት ጊዜ ገደብ ለማጠናቀቅ እንደሚሰራና ከ360 በላይ ሰዎች ሥራ መፍጠሩን ተናግረዋል።

ግንባታው በሚካሄድበት ቀበሌ 09 ጠባሴ ሽፍኑ ገብርኤል ጎጥ አርሶ አደር ጌታቸዉ ሸዋ ፈራ በሰጡት አስተያየት ድርጅቱ ትምህርትን ለማስፋፋትያዘውን ዓላማ ለማሳካት ድጋፍ እንደሚያደርጉ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም